መጽሐፈ ምሳሌ 25
25
ሌሎች የሰሎሞን ምሳሌዎች
1እነዚህ ሌሎች የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው፤ እነርሱም በእጅ የተጻፉት በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቤተ መንግሥት በነበሩ ሰዎች አማካይነት ነበር።
2እግዚአብሔር የምሥጢር አምላክ ስለ ሆነ እናከብረዋለን፤ ነገሥታትን የምናከብራቸው ነገሮችን መርምረው በመግለጣቸው ነው።
3ንጉሥ የሚያስበውን ማወቅ አትችልም፤ የንጉሥ አሳብ እንደ ሰማይ የመጠቀ እንደ ውቅያኖስ የጠለቀ ነው።
4ከብር ዝገትን አስወግድ፤ ከዚያ በኋላ አንጥረኛ ያሳምረዋል። 5ከንጉሥ ፊት ክፉ ሰዎችን አስወግድ፤ መንግሥቱም በፍትሕ ጸንታ ትኖራለች።
6በንጉሥ ፊት በምትቆምበት ጊዜ ዝነኛ ለመሆን አትሞክር፤ ወደ ታላላቅ ሰዎችም ደረጃ ከፍ ለማለት አትፈልግ። 7ከአንተ ለበለጠ ሰው ስፍራህን እንድትለቅ በሹም ፊት ተጠይቀህ ከምታፍር ይልቅ “ና ወደ ላይ ከፍ በል!” ብትባል ይሻልሃል። #ሉቃ. 14፥8-10።
8አንተ ከመሰከርክ በኋላ ሌላ ሰው ምስክርነትህ የተሳሳተ መሆኑን የገለጠ እንደሆን ስለምታፍር ስለ አየኸው ነገር ለመመስከር ፈጥነህ ወደ ሸንጎ አትሂድ።
9በአንተና በባልንጀራህ መካከል ክርክር ቢነሣ ከእርሱ ጋር ተወያይተህ አለመግባባትህን አስወግድ እንጂ የሌላን ሰው ምሥጢር አታውጣ። 10አለበለዚያ ምሥጢር የማትጠብቅ መሆንክን የሚያውቅ ሰው ያዋርድሃል፤ ሊለወጥ የማይችልም መጥፎ ስም ይሰጥሃል።
11በወቅቱ በትክክል የተነገረ ቃል በብር ጻሕል ላይ እንደ ተቀመጠ ወርቅ ውበት ይኖረዋል።
12ለማዳመጥ ፈቃደኛ ለሆነ ሰው ብልኅ ሰው የሚሰጠው ተግሣጽ ከወርቅ ጉትቻ ወይም ከጥሩ ወርቅ ከተሠራ ጌጥ ይበልጥ የተወደደ ይሆንለታል።
13ቀዝቃዛ ውሃ በሙቀት ጊዜ የሚያረካውን ያኽል ታማኝ መልእክተኛም የላከውን ሰው ያረካል።
14የማይሰጠውን ነገር “እሰጣለሁ” እያለ የሚመካ ሰው ዝናብ እንደሌለው ደመናና ነፋስ ነው።
15በትዕግሥት ማግባባት ታላቅ ተቃውሞን ያበርዳል፤ መሪዎችን ሳይቀር በሐሳብ እንዲስማሙ ያደርጋል።
16ሲበዛ እንዳያስጠላህ ከሚያስፈልግህ በላይ ብዙ ማር. አትብላ፤ 17ወደ ጐረቤትህ ቤት አዘውትረህ አትሂድ፤ ሊሰለችህና ሊጠላህ ይችላል።
18በባልንጀራው ላይ በሐሰት የሚመሰክር ሰው የሰይፍ፥ የዱላና የተሳለ ፍላጻ ያኽል ሊጐዳው ይችላል።
19በመከራ ጊዜ በማይታመን ሰው ላይ መደገፍ በተነቃነቀ ጥርስ እንደማኘክና በተሰበረ እግር እንደ መራመድ ያኽል ነው።
20ላዘነ ሰው መዝፈን፥ በብርድ ቀን ልብስ የማውለቅና በቊስል ላይ ሆምጣጤ የመጨመር ያኽል የከፋ ነው።
21ጠላትህ ቢርበው አብላው፤ ቢጠማውም አጠጣው፤ 22ይህን ብትፈጽም በኀፍረት እሳት እንዲቃጠል ታደርገዋለህ፤ ለአንተ ግን እግዚአብሔር የመልካም ሥራህን ዋጋ ይከፍልሃል። #ሮም 12፥20።
23የሰሜን ነፋስ ዝናብን እንደሚያመጣ ሐሜትም ቊጣን ማስከተሉ የተረጋገጠ ነው።
24ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር ይልቅ በጣራ ማእዘን ላይ መኖር ይሻላል።
25ከሩቅ አገር የመጣ መልካም ዜናን መስማት የደከመው ሰው ቀዝቃዛ ውሃ ጠጥቶ የሚረካውን ያኽል ያስደስታል።
26የክፉን ሰው ጠባይ የሚወርስ ደግ ሰው የደፈረሰን ምንጭ ወይም የተመረዘን ኲሬ ይመስላል።
27ብዙ ማር. መብላት መልካም አይደለም፤ እንዲሁም ከሰው ክብርን ለማግኘት መፈለግ አያስከብርም።
28ቊጣህን መቈጣጠር ባትችል መከላከያ አጥር እንደሌላትና ለጠላት ተጋልጣ እንደምትገኝ ከተማ ትሆናለህ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 25: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997