መጽሐፈ ምሳሌ 24
24
-19-
1በክፉ ሰዎች አትቅና፤ ከእነርሱም ጋር ጓደኛ ለመሆን አትፈልግ፤ 2እነርሱ ዘወትር በአእምሮአቸው ግፍን ያቅዳሉ፤ በአንደበታቸውም ይሸነግላሉ።
-20-
3በጥበብ ቤት ይሠራል፤ በማስተዋልም ጸንቶ እንዲኖር ይደረጋል። 4ዕውቀት ሲኖር ቤት በከበሩና በሚያምሩ ዕቃዎች ይሞላል።
-21-
5ብርቱ ከመሆን ይልቅ ብልኅ መሆን ይሻላል፤ በእርግጥም ዕውቀት ከኀይል ይበልጣል፤ 6ለጦርነት ከመሰለፍህ በፊት በጥንቃቄ ዕቅድ ማውጣት ይኖርብሃል፤ ብዙ አማካሪዎች የምታገኝ ከሆነም ማሸነፍህ አይቀርም።
-22-
7ማስተዋል የጐደለው ሰው ጥበብን መገንዘብ አይችልም፤ ሰዎች ቁም ነገር ባለው ጉዳይ ላይ ሲወያዩ እርሱ የሚያቀርበው አስተያየት የለም።
-23-
8ዘወትር ክፋትን ለማድረግ የሚያሤር ሁሉ “ተንኰለኛ” የሚል የቅጽል ስም ይወጣለታል፤ 9ሞኝ ሁልጊዜ የሚያስበው ኃጢአትን ስለ ማድረግ ነው፤ ፌዘኛን ሰዎች ሁሉ ይጠሉታል።
-24-
10መከራ በሚደርስብህ ጊዜ መጽናት የማትችል ከሆንክ ምንም ብርታት የለህም ማለት ነው።
-25-
11በግፍ ወደ ሞት የሚወሰዱትን ሰዎች ታደግ፤ ለመገደል እያዳፉ ከሚወስዱአቸው ሰዎች እጅ አድን። 12ምናልባት “እኔ አላውቀውም” ትል ይሆናል፤ ነገር ግን ልብን የሚመረምር አያስተውለውምን? እርሱ ሕይወትህን የሚጠብቅ እርሱ አያውቀውምን? እያንዳንዱንስ እንደ ሥራው አይከፍለውምን?
-26-
13ልጄ ሆይ! መልካም ስለ ሆነ ማር. ብላ፤ የማር ወለላ ለምላስህ ጣፋጭ ነው። 14ጥበብም ለነፍስህ መልካም መሆኑን ዕወቅ፤ ጥበብን ብታገኝ የወደፊት ኑሮህ የተቃና ይሆናል፤ ተስፋህም አያቋርጥም።
-27-
15እንደ ዐመፀኛ ሰው የጻድቁን ሰው ቤት ለመዝረፍ አትሸምቅ፤ መኖሪያውንም አትውረር። 16ጻድቅ ሰው ሰባት ጊዜ ቢወድቅ እንኳ እንደ ገና ይነሣል፤ ዐመፀኞች ግን ጥፋት ይደርስባቸዋል።
-28-
17ጠላትህ ሲሰናከል ደስ አይበልህ፤ በሚወድቅበትም ጊዜ ሐሤት አታድርግ፤ 18በዚህ ነገር ደስ ቢልህ ግን እግዚአብሔርን ታሳዝናለህ፤ እግዚአብሔርም በጠላትህ ላይ የሚያሳየውን ቊጣ ያቆማል።
-29-
19በክፉ ሰዎች አድራጎት አትጨነቅ፤ በእነርሱም አትቅና፤ 20ዐመፀኛ ሰው “ወደ ፊት ይህን አገኛለሁ” ብሎ ተስፋ የሚያደርገው ነገር የለውም።
-30-
21ልጄ ሆይ! እግዚአብሔርን ፍራ ንጉሥንም አክብር፤ በእነርሱም ላይ ከሚያምፁ ሰዎች ጋር አትተባበር። 22በእነዚህ ዐመፀኞች ላይ ታላቅ ጥፋት ይደርስባቸዋል፤ የሚደርስባቸው ጥፋት ግን ምን ዐይነት እንደ ሆነ ማን ያውቃል?
ተጨማሪ የጥበብ ምክሮች
23የጥበበኞች ተጨማሪ አባባሎች፦
በዳኝነት ማዳላት ስሕተት ነው፤ 24በደለኛውን ንጹሕ የሚያደርግን ዳኛ፥ ሰዎች ይረግሙታል፤ ሕዝቦችም ያወግዙታል። 25በደለኛውን በትክክል የሚቀጡ ዳኞች ግን መልካም ይሆንላቸዋል፤ ብዙ በረከትም ያገኛሉ።
26ትክክለኛ መልስ የሚሰጥ ሰው እንደ ልብ ወዳጅ ይቈጠራል።
27በመጀመሪያ በርስትህ ላይ ለኑሮህ የሚያስፈልግህን ሁሉ አደራጅ፤ ከዚያ በኋላ ቤት ሥራ።
28በማንም ሰው ላይ ያለ በቂ ምክንያት አትመስክር፤ በእርሱም ላይ አሳሳች ቃል አትናገር። 29“ሰው ክፉ ነገር በሚያደርግብኝ መጠን እኔም ክፉ ነገር አደርግበታለሁ! የበቀል ብድራቴንም እመልሳለሁ!” አትበል።
30በሰነፍና ማስተዋል በጐደለው ሰው እርሻ ውስጥ በወይኑም አትክልት ቦታ ሄድኩኝ፤ 31በአረምና በቊጥቋጦ ተሞልቶ ነበር፤ በዙሪያውም ያለ የግንብ አጥር ፈርሶአል። 32ይህን በተመለከትኩ ጊዜ ስለ እርሱ አስባለሁ፤ ከተመለከትኩትም ነገር ትምህርትን ገበየሁ። 33ብትፈልግ ትንሽ ሸለብ ያድርግህ፤ ጥቂት እንቅልፍም ይውሰድህ፤ እጆችህንም አጣምረህ ለጥቂት ጊዜ ዐረፍ በል። 34ነገር ግን ገና ተኝተህ ሳለህ ድኽነትና ማጣት የጦር መሣሪያ እንደ ታጠቀ ወንበዴ በድንገት እንደሚደርሱብህ ዕወቅ። #ምሳ. 6፥10-11።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 24: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997