መጽሐፈ ምሳሌ 23
23
-6-
1ከባለ ሥልጣን ጋር ለመመገብ በአንድ ገበታ ላይ ብትቀርብ ማንነቱን አትዘንጋ፤ 2ለመብላት ብትጓጓ እንኳ ብዙ ከመብላት ተቈጠብ። 3ምናልባት ሊታዘብህ ስለሚችል የሚያቀርብልህን መልካም ምግብ ተስገብግበህ አትብላ።
-7-
4ለመበልጸግ አትድከም፤ ከዚህ ዐይነት ስግብግብነት ለመራቅ ጥበበኛ ሁን፤ 5እንዲህ ዐይነቱ ሀብት እያየኸው ወዲያው ይጠፋል፤ በሰማይ እንደ ሚበርር ንስር ክንፍ አውጥቶ ይበራል።
-8-
6የስስታምን እንጀራ አትብላ፤ የሚያቀርብልህም ጥሩ ምግብ አያስጐምጅህ፤ 7ከልቡ ሳይሆን ምግቡን እንድትተውለት ፈልጎ ለማስመሰል ያኽል “ብላ፥ ጠጣ” ይልሃል። 8የበላኸውን እንኳ ትተፋዋለህ፤ እርሱን በማቈላመጥ የተናገርከውም ቃል ከንቱ ይሆናል።
-9-
9ጥበብ የሞላበት ምክርህን ስለሚንቅብህ ለሞኝ ሰው ቁም ነገር አታጫውተው፤
-10-
10የቈየውን የወሰን ምልክት አትለውጥ፤ እንዲሁም አባትና እናት የሌላቸውን ልጆች መሬት አትቀማ፤ 11እግዚአብሔር ጽኑ መከታቸው ስለ ሆነ ለእነርሱ ይከራከርላቸዋል።
-11-
12አእምሮህን በትምህርት ላይ፥ ጆሮህንም ዕውቀትን በመስማት ላይ አውላቸው።
-12-
13ልጅን በሥነ ሥርዓት ከመቅጣት አትቦዝን፤ በአርጩሜ ብትመታው አይሞትም፤ 14እንዲያውም በአርጩሜ ብትመታው ሕይወቱን ከሞት ለማዳን ጥሩ ዋስትና ይሆነዋል።
-13-
15ልጄ ሆይ! ጠቢብ ብትሆን በጣም ደስ ይለኛል፤ 16ትክክለኛ ቃል በምትናገርበት ጊዜ ኲራት ይሰማኛል።
-14-
17በኃጢአተኞች ላይ አትቅና፤ እግዚአብሔርን መፍራት የዘወትር ሐሳብህ ይሁን፤ 18ይህን ብታደርግ የወደፊት ኑሮህ የተቃና ይሆናል፤ ተስፋህም አያቋርጥም።
-15-
19ልጄ ሆይ! አድምጥ፤ ብልኅም ሁን፥ ከእግዚአብሔርም መንገድ ፈቀቅ አትበል፤ 20ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡና ብዙ ምግብ ከሚበሉ ጋር ጓደኛ አትሁን፤ 21ሰካራሞችና ሆዳሞች ይደኸያሉ፤ ሙያው ማንቀላፋት ብቻ የሆነ ሰውም ደኽይቶ ቡትቶ ለባሽ ይሆናል።
-16-
22የወለደህ እርሱ ስለ ሆነ የአባትህን ምክር ስማ፤ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት።
23እውነትን፥ ጥበብን፥ ተግሣጽን፥ ማስተዋልን ገንዘብ አድርጋቸው እንጂ አትተዋቸው። 24የጨዋ ልጅ አባት ታላቅ ደስታ ይሰማዋል፤ ብልኅ ልጅ የወለደም ሰው ኲራት ይሰማዋል። 25አባትህና እናትህ በአንተ ደስ ይበላቸው፤ እናትህም በአንተ ሐሤት ታድርግ።
-17-
26ልጄ ሆይ፥ በጥንቃቄ አድምጠኝ፤ የእኔ አኗኗር ምሳሌ ይሁንህ፤ 27ሴትኛ ዐዳሪዎችና ባለጌ ሴቶች እንደ ጒድጓድ ወጥመድ ወደ ሞት የሚያደርሱ ናቸው። 28እንደ ወንበዴ አድብተው ይጠብቁሃል፤ ብዙ ወንዶችን በሕጋዊ ጋብቻ ታማኝ ሆነው እንዳይኖሩ አድርገዋል።
-18-
29ሐዘንና ትካዜ የሚደርስበት ማን ነው? ዘወትር ክርክርና ጭቅጭቅ የሚያነሣሣ ማን ነው? ምክንያቱን ሳያውቅ ተፈንክቶ የሚገኝ ማን ነው? ዐይኑ የሚቀላበት ማን ነው? 30ይህ ሁሉ ነገር የሚደርሰው ብዙ የወይን ጠጅ በመጠጣትና ድብልቅ የሆኑ ጠንካራ መጠጦችን በመለማመድ ጊዜውን በሚያባክን ሰው ላይ ነው። 31ስለዚህ ምንም እንኳ መልኩ በጣም ቀይ ሆኖ በብርጭቆ ውስጥ ቢያንጸባርቅ ሲጠጡትም ሰተት ብሎ ቢገባ የወይን ጠጅ አያስጐምጅህ። 32በመጨረሻ እንደ እባብ ይነድፍሃል፤ እንደ እፉኝትም መርዙን ይረጭብሃል፤ 33ዐይንህ ብዥ ብዥ ስለሚልብህ አዳዲስ ነገሮችን የምታይ ይመስልሃል፤ በትክክል ማሰብም ሆነ መናገር አትችልም። 34በባሕር ውስጥ ያለህና ማዕበል ከሚያንገላታት መርከብ ምሰሶ ላይ የተወዳጀህ ይመስልሃል። 35እንዲሁም “ተደብድቤአለሁ፤ ነገር ግን አልተጐዳሁም፤ ተመትቼአለሁ፤ ሕመሙ ግን አልተሰማኝም፤ መቼ ነው የምነቃው? ሌላ ተጨማሪ መጠጥ የምጠጣው መቼ ይሆን?” ትላለህ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 23: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997