ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2
2
የክርስቶስ ትሕትና ምሳሌነት
1በክርስቶስ መበረታታት ካላችሁ፥ በፍቅሩም የተጽናናችሁ ከሆነ፥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ኅብረት ካላችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ደግነትንና ርኅራኄን ካሳያችሁ፥ 2ስለዚህ በሐሳብ፥ በፍቅር፥ በመንፈስ፥ በዓላማ እየተስማማችሁ ደስታዬ የተሟላ እንዲሆን አድርጉ። 3በትሕትና ተሞልታችሁ ሌሎች ሰዎች ከእናንተ እንደሚሻሉ አድርጋችሁ ቊጠሩ እንጂ በራስ ወዳድነት ወይም “ያለ እኔ ማን አለ” በሚል ትምክሕት ምንም ነገር አታድርጉ። 4እንዲሁም እያንዳንዱ የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ። 5በዚህ ዐይነት ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየው የትሕትና ሥራ በእናንተም ሕይወት ሊኖር ይገባል።
6እርሱ ሁልጊዜ የመለኮት ባሕርይ አለው።
ይሁን እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የሚያደርገውን
የመለኮት ባሕርይ በኃይል እንደ ያዘ አልቈጠረውም።
7ይልቁንም ያለውን ክብር ሁሉ ትቶ
እንደ ባሪያ ሆኖ ታየ
እንደ ሰውም ተወለደ፤
በሰው አምሳልም ተገለጠ፤
8በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤
እስከ ሞት ድረስ፥
ያውም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ
ታዛዥ ሆነ።
9በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ወዳለው
የክብር ስፍራ ከፍ አደረገው፤
ከስም ሁሉ የሚበልጠውንም ስም ሰጠው።
10ስለዚህ ለኢየሱስ ስም ክብር፥
በሰማይና በምድር፥ ከምድር በታችም ያሉት ሁሉ
በጒልበታቸው ይንበረከካሉ።
11በአንደበታቸውም
“ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” ብለው በመመስከር
ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሰጣሉ። #ኢሳ. 45፥23።
ለዓለም ሰዎች እንደ ብርሃን ማብራት
12ወዳጆቼ ሆይ! እኔ ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ሁልጊዜ ታዛዦች እንደ ነበራችሁ፥ ይልቁንም አሁን ከእናንተ በራቅሁበት ጊዜ ይበልጥ ታዛዦች እንድትሆኑ አሳስባችኋለሁ፤ ስለዚህ እያንዳንዳችሁ መዳናችሁን ፍጹም ለማድረግ በፍርሃትና በአክብሮት ተግታችሁ ሥሩ። 13እግዚአብሔር ታዛዥነትን ለእናንተ እየሰጠ ዓላማውን ከፍጻሜ ለማድረስ በእናንተ ውስጥ ይሠራል።
14ማናቸውንም ሥራ በምትሠሩበት ጊዜ አታጒረምርሙ ወይም አትከራከሩ። 15ይህም ከሆነ በዚህ በጠማማና በመጥፎ ትውልድ መካከል ነውርና ነቀፋ የሌለባችሁ ንጹሓን የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን በዚህ ዓለም እንደ ከዋክብት ታበራላችሁ። #ዘዳ. 32፥5። 16ይህም የሚሆነው ሕይወት የሚገኝበትን ቃል ሳታቋርጡ አጥብቃችሁ በመያዝ ነው፤ በዚህ ዐይነት ሩጫዬም ሆነ ሥራዬ ከንቱ ሆኖ ስለማይቀር ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የምመካበት ምክንያት ይኖረኛል ማለት ነው።
17ለእግዚአብሔር በእምነት በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ የእኔም ሕይወት ተጨማሪ መሥዋዕት ሆኖ ቢቀርብ እንኳ ደስ ይለኛል፤ እናንተም የደስታዬ ተካፋዮች ትሆናላችሁ። 18እንዲሁም እናንተ ተደስታችሁ እኔንም የደስታችሁ ተካፋይ ታደርጉኛላችሁ።
የጢሞቴዎስና የኤጳፍሮዲቱስ አገልግሎት
19እኔ ስለ እናንተ ሁኔታ በመስማት እንድጽናና ጢሞቴዎስን በፍጥነት ወደ እናንተ ለመላክ እንደሚያስችለኝ በጌታ ኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። 20ስለ እናንተ ሁኔታ ከልብ የሚያስብ ከጢሞቴዎስ በቀር ሌላ ሰው የለኝም። 21ሌሎቹ ግን የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ያሳድዳሉ እንጂ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ግድ የላቸውም። 22ጢሞቴዎስ፥ ታማኝነቱ ተፈትኖ የተመሰከረለት መሆኑንና ከእኔም ጋር እንደ አባትና ልጅ ተባብረን ወንጌልን በማስተማር አብረን ስንሠራ መቈየታችንን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 23ስለዚህ የእኔ ጉዳይ ከምን እንደሚደርስ ከተረዳሁ በኋላ ጢሞቴዎስን በፍጥነት ወደ እናንተ እንደምልክላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። 24እንዲያውም እኔ ራሴ በቶሎ ወደ እናንተ መምጣት እንድችል ጌታ ይረዳኛል ብዬ እተማመናለሁ።
25እንዲሁም እኔን በሚያስፈልገኝ ሁሉ እንዲረዳኝ ልካችሁት የነበረውን ወንድሜን ኤጳፍሮዲቱስን ወደ እናንተ መላክ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ እርሱ ከእኔ ጋር የተሰለፈ ወታደርና የሥራ ጓደኛዬ ሆኖ ሲሠራ የቈየ ነው። 26እርሱን ወደ እናንተ የምልከውም ሁላችሁንም ለማየት በመናፈቁና እናንተም መታመሙን በመስማታችሁ ስለ ተጨነቀ ነው። 27በእርግጥ በጠና ታሞ ለሞት ተቃርቦ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ምሕረት አደረገለት፤ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ሐዘን በሐዘን ላይ እንዳይደራረብብኝ ለእኔም ጭምር ምሕረት አደረገ። 28ስለዚህ እናንተ እርሱን በማየት እንድትደሰቱና የእኔም ሐዘን እንዲቃለል እርሱን ወደ እናንተ ልልከው በይበልጥ ፈለግኹ። 29እንግዲህ በጌታ አማኝ እንደ መሆኑ በደስታ ተቀበሉት፤ እንደ እርሱ ያሉትንም ሰዎች ሁሉ አክብሩአቸው። 30እናንተ በቅርብ ተገኝታችሁ ልታደርጉልኝ ያልቻላችሁትን ርዳታ እርሱ ለማሟላት ብሎ ስለ ክርስቶስ ሥራ ለሕይወቱ ሳይሳሳ ለሞት ተቃርቦ ነበር።
Currently Selected:
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997