ኦሪት ዘኊልቊ 9
9
ሁለተኛው የፋሲካ በዓል
1የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ምድረ በዳ እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2“እስራኤላውያን የፋሲካውን በዐል በተወሰነለት ጊዜ ያክብሩ፤ 3በዚህ ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት በሕጉና በሥርዓቱ መሠረት ሥርዓቱን ይፈጽሙ።” 4ስለዚህ ሙሴ የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ ለሕዝቡ ነገራቸው፤ 5እነርሱም የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን በምሽት በሲና ምድረ በዳ በዓሉን አከበሩ፤ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሁሉን ነገር አደረጉ። #ዘፀ. 12፥1-13።
6ነገር ግን በድን ከመንካታቸው የተነሣ ያልነጹ ጥቂት ሰዎች ስለ ነበሩ በዚያን ቀን የፋሲካን በዓል ማክበር አልቻሉም፤ ስለዚህ እነርሱ ወደ ሙሴና አሮን ዘንድ ቀርበው እንዲህ አሉ፤ 7“እኛ በድን በመንካታችን ረክሰናል፤ ነገር ግን ከቀሩት እስራኤላውያን ተለይተን በወቅቱ ለእግዚአብሔር መባ እንዳናቀርብ ስለምን እንከለከላለን?”
8ሙሴም “ከእግዚአብሔር መመሪያ እስክቀበል ድረስ ጠብቁ” አላቸው።
9እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 10“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ከእናንተም ሆነ ከዘራችሁ ሰዎች በድን በመንካት ቢረክሱ ወይም ወደ ሩቅ አገር ለመሄድ በጒዞ ላይ ቢሆኑና የፋሲካን በዓል ለማክበር ቢፈልጉ፥ 11ዘግይተው ሁለተኛው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት እንዲያከብሩ ተፈቅዶላቸዋል፤ ሲያከብሩም እርሾ የሌለበትን ቂጣ ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉ። 12እስከ ማግስቱ ጠዋት ድረስ ከዚያ ምግብ አስተርፈው አያሳድሩ፤ ከእንስሳውም አጥንት አንዱንም አይስበሩ፤ በተሰጣቸው የሥርዓት መመሪያ መሠረት በዓሉን ያክብሩ፤ #ዘፀ. 12፥46፤ ዮሐ. 19፥36። 13ንጹሕ የሆነ እና ወደ ሩቅ አገር ያልሄደ ማንኛውም ሰው የፋሲካን በዓል በወቅቱ ባያከብር ከሕዝቤ ይለይ፤ መባውን በተወሰነው ጊዜ ባለማቅረቡ፥ ስለ ኃጢአቱ ተገቢውን ቅጣት ይቀበላል።
14“በእናንተ መካከል መጻተኛ የእግዚአብሔርን ፋሲካ በዓል ለማክበር ቢፈልግ በተወሰነው ደንብና የሥርዓት መመሪያ ሁሉ መሠረት ማክበር ይኖርበታል፤ የአገር ተወላጁም ሆነ መጻተኛ ይህን ደንብ በተመሳሳይ ሁኔታ ይፈጽም።”
በእሳት አምሳል የታየው ደመና
(ዘፀ. 40፥34-38)
15የመገናኛው ድንኳን በተተከለበት ቀን ደመናው ድንኳኑን ሸፈነው፤ ከማታ ጀምሮ እስከ ጠዋት ድረስ በድንኳኑ ላይ እንደ እሳት ያበራ ነበር፤ 16በቀን ደመና ይሸፍነው ነበር፤ ደመናውም በሌሊት እንደ እሳት ያበራ ነበር። 17ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሣበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ሰፈራቸውን ለቀው ይጓዙ ነበር፤ ደመናውም በሚወርድበት ቦታ እንደገና ይሰፍሩ ነበር፤ 18እስራኤላውያንም ከሰፈር የሚለቁትም ሆነ በሌላ ቦታ የሚሰፍሩት በእግዚአብሔር ትእዛዝ ነበር፤ ደመናው በድንኳኑ ላይ ዐርፎ እስከ አለ ድረስ በአንድ ሰፈር ይቈያሉ፤ 19ደመናው በድንኳኑ ላይ ለብዙ ቀኖች ቢቈይ እንኳ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ እዚያው ይቈያሉ እንጂ አይንቀሳቀሱም። 20አንዳንድ ጊዜ ደመናው በድንኳኑ ላይ የሚቈይ ለጥቂት ቀኖች ብቻ ነበር፤ ያም ሆነ ይህ በሰፈር የሚቈዩትም ሆነ ወደ ፊት የሚሄዱት በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት ነበር፤ 21አንዳንድ ጊዜ ደመናው የሚቈየው ከምሽት እስከ ንጋት ብቻ ነበር፤ ስለዚህ ደመናው እንደ ተነሣ ወዲያውኑ ጒዞ ይቀጥላሉ፤ ወይም ደመናው ቀንና ማታ ቢቈይ ደመናው ሲነሣ ይሄዱ ነበር። 22ሁለት ቀንም ይሁን አንድ ወር፥ አንድ ዓመትም ይሁን ከዚያ የረዘመ ጊዜ ደመናው በድንኳኑ ላይ እስካረፈበት ጊዜ ድረስ አይንቀሳቀሱም ነበር፤ ደመናው ሲነሣ ግን ጒዞአቸውን ይቀጥሉ ነበር። 23ድንኳናቸውን የሚተክሉትም ሆነ ሰፈር ለቀው ወደ ፊት የሚጓዙት እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነበር።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 9: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997