ኦሪት ዘኊልቊ 32:20-42

ኦሪት ዘኊልቊ 32:20-42 አማ05

ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ይህ የተናገራችሁት ሁሉ እውነት ከሆነ እዚህ በእግዚአብሔር ፊት ወደ ጦርነት ለመሄድ ተዘጋጁ። የጦር ሰዎቻችሁ ሁሉ ዮርዳኖስን መሻገር፥ በእግዚአብሔር አዛዥነት በጠላቶቻችን ላይ መዝመት፥ እግዚአብሔር ድል አድርጎ፥ ምድራቸውን እስኪወስድ ድረስ መዋጋት አለባቸው፤ ይህን ካደረጋችሁ በኋላ መመለስ ትችላላችሁ፤ በዚያን ጊዜ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለወገኖቻችሁ ለእስራኤላውያን ያለባችሁን ግዴታ ትወጣላችሁ፤ ከዚያ በኋላ ይህ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያለው ምድር የእናንተ ርስት መሆኑን እግዚአብሔር ያረጋግጥላችኋል። ቃላችሁን ባትጠብቁ ግን እግዚአብሔርን የምታሳዝኑ ሆናችሁ እንዳትገኙ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ ሰለ ኃጢአታችሁም ቅጣት የሚደርስባችሁ መሆኑንም አትዘንጉ። ስለዚህ ከተሞቻችሁንና ለእንስሶቻችሁ የሚሆኑትን በረቶች ሥሩ፤ ነገር ግን የገባችሁትንም የተስፋ ቃል ፈጽሙ።” የጋድና የሮቤል ወገኖች እንዲህ አሉ፤ “እኛ አገልጋዮችህ፥ አንተ ጌታችን እንዳዘዝከው እናደርጋለን። ሚስቶቻችንና ልጆቻችን፥ ከብቶቻችንና በጎቻችን፥ በዚህ በገለዓድ ከተሞች ይቈያሉ፤ ነገር ግን እኛ አገልጋዮችህ ለጦርነት የታጠቅን ሁሉ በእግዚአብሔር መሪነት ለመዋጋት ልክ አንተ ጌታችን እንደምታዘን ወደ ማዶ እንሻገራለን።” ስለዚህም ሙሴ ስለ እነርሱ ለካህኑ ለአልዓዛር፥ ለነዌ ልጅ ለኢያሱና ለእስራኤል ሕዝብ የነገድ አለቆች ሁሉ ይህን ትእዛዝ አስተላለፈ። “የጋድና የሮቤል ሰዎች ዮርዳኖስን ተሻግረው በእግዚአብሔር መሪነት ለጦርነት የሚዘጋጁ ከሆነና በእነርሱም ርዳታ ምድሪቱን የምትወርሱ ከሆነ የገለዓድን ምድር ለእነርሱ ርስት አድርጋችሁ ስጡአቸው። ዮርዳኖስን ተሻግረው ከእናንተ ጋር ወደ ጦርነት የማይሄዱ ከሆነ ግን ልክ እንደ እናንተው በከነዓን ምድር የራሳቸው ድርሻ የሆነ ርስት ይሰጣቸው።” የጋድና የሮቤል ሰዎችም እንዲህ ሲሉ መልስ ሰጡ፤ “እግዚአብሔር ያዘዘንን ሁሉ እናደርጋለን፤ በእርሱም መሪነት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፤ በዚህ በዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን የርስት ድርሻችንን ለራሳችን ለማስቀረት ወደ ጦርነት እንሄዳለን።” ስለዚህ ሙሴ የአሞራውያንን ንጉሥ የሲሖንንና የባሳንን ንጉሥ የዖግን ግዛት በዙሪያቸው ያሉትን ከተሞችና አገሮች ጭምር ለጋድና ለሮቤል ነገዶች እንዲሁም ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠ፤ የጋድ ነገድ የተመሸጉትን የዲቦንን፥ የዐጣሮትን፥ የዓሮዔርን፥ የዓጥሮት ሶፋንን፥ የያዕዜርን፥ የዮግበሃን፥ የቤትኒምራንና የቤትሃራንን ከተሞች በማደስ ለከብቶቹም በረቶችን ሠራ። የሮቤል ነገድ የሐሴቦንን፥ የኤልዓሌን፥ የቂርያታይምን፥ የነቦን፥ በኋላ ስሙ የተለወጠው የባዓልመዖንንና የሲብማን ከተሞች አደሰ፤ እነርሱም ላደሱአቸው ከተሞች ሁሉ አዲስ ስም አወጡላቸው። የምናሴ ልጅ የማኪር ቤተሰብ የገለዓድን ምድር በመውረር ወረሰ፤ በዚያም ይኖሩ የነበሩትን አሞራውያንን አባረረ። ስለዚህም ሙሴ የገለዓድን ምድር ለማኪር ቤተሰብ ሰጣቸው፤ እነርሱም በዚያ ኖሩ። ከምናሴ ነገድ የሆነው ያኢር በአንዳንድ መንደሮች ላይ አደጋ ጥሎ ወሰዳቸው፤ “የያኢር መንደሮች” ብሎም ሰየማቸው። ኖባሕ ደግሞ በቄናትና በመንደሮችዋ ላይ አደጋ በመጣል ወሰዳቸው፤ በራሱም ስም “ኖባሕ” ብሎ ሰየማቸው።