የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 25

25
ሞአባውያን እስራኤላውያንን ማሳታቸው
1የእስራኤል ሕዝብ በሺጢም ሸለቆ ሰፍሮ በነበረበት ጊዜ ወንዶቹ እዚያ ከነበሩበት ሞአባውያን ሴቶች ጋር አመነዘሩ፤ 2እነዚያም ሴቶች ለሞአብ ጣዖት የተሠዋውን መሥዋዕት እንዲመገቡ ጋበዙአቸው፤ እስራኤላውያንም የመሥዋዕቱን ምግብ በልተው ፔዖር በሚባለው ተራራ ላይ ለሚገኘው በዓል ለተባለውም ጣዖት ሰገዱ፤ 3በዚህም ዐይነት እስራኤላውያን በፔዖር ለባዓል ጣዖት በመስገዳቸው እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ተቈጣ። 4እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በእስራኤል ላይ የነደደው ቊጣዬ ይበርድ ዘንድ የእስራኤልን መሪዎች ሁሉ ወስደህ በጠራራ ፀሐይ በሕዝብ ፊት ግደላቸው።” 5ሙሴም ለእስራኤል መሪዎች “እያንዳንዳችሁ ከየነገዳችሁ በዓል ለሚባለው የፒዖር ጣዖት የሰገደውን ሰው ሁሉ ግደሉ” ብሎ ትእዛዝ አስተላለፈ።
6ሙሴና መላው ማኅበር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተገኝተው በሚያለቅሱበት ጊዜ ከእስራኤላውያን አንዱ አንዲት ምድያማዊት ሴት ይዞ በእነርሱ ፊት በማለፍ ወደ ቤተሰቡ አቀረባት። 7የካህኑ የአሮን የልጅ ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ይህን ባየ ጊዜ ከተቀመጠበት በመነሣት ከጉባኤው መካከል ወጥቶ ሄደ፤ ጦርም አንሥቶ፥ 8ሰውየውና ሴቲቱ ወዳሉበት ድንኳን ገባ፤ ሁለቱንም በአንድነት በጦር ወግቶ ገደላቸው፤ በዚህም ዐይነት እስራኤላውያንን በማጥፋት ላይ የነበረው መቅሠፍት ቆመ፤ 9ነገር ግን እስከዚያው ሰዓት ድረስ ያ መቅሠፍት ኻያ አራት ሺህ ሕዝብ አጥፍቶ ነበር።
10እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 11“የካህኑ የአሮን የልጅ ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባደረገው ነገር ምክንያት በእስራኤል ሕዝብ ላይ ያለኝ ቊጣ በርዶአል፤ ፊንሐስ ከእኔ በቀር ለሌላ አምላክ የሚሰግዱትን መታገሥ አልፈለገም፤ በቊጣዬ እስራኤልን ያላጠፋሁትም እርሱ ስለ እኔ ባሳየው ቅናት ነው። 12ስለዚህ እኔ ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም ጸንቶ የሚኖር የሰላም ቃል ኪዳኔን የምሰጠው መሆኔን ንገረው። 13እርሱ ለእኔ ለአምላኩ ቀናተኛ በመሆኑና የሕዝቡንም ኃጢአት በማስተስረዩ እርሱና ዘሮቹ በሙሉ ለዘለዓለም ካህናት ይሆናሉ።”
14ከምድያማዊቱ ሴት ጋር የተገደለው እስራኤላዊ ስም የሳሉ ልጅ ዚምሪ ሲሆን እርሱም በስምዖን ነገድ ውስጥ የጐሣ አለቃ ነበር። 15የሴቲቱም ስም ኮዝቢ ይባል ነበር፤ “ጹር” ተብሎ የሚጠራው አባትዋም በአንድነት የሚኖሩ የጥቂት ምድያማውያን ጐሣዎች አለቃ ነበር።
16እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 17“በምድያማውያን ላይ አደጋ ጥላችሁ ደምስሱአቸው፤ 18ይህንንም የምታደርጉት እናንተን በፔዖር በማታለል ግፍ ስለ ሠሩባችሁና በፔዖር በወረደው መቅሠፍት ምክንያት በተገደለችው በአለቃቸው ልጅ በኮዝቢ አማካይነት በፈጸሙት ሽንገላ ነው።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ