የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ናሆም 2

2
የነነዌ አወዳደቅ
1ነነዌ ሆይ! አደጋ ጣይ መጥቶብሻል!
ስለዚህ ምሽጎችሽን አጠናክሪ!
አውራ መንገዱን ሁሉ ጠብቂ! ወገብሽን ታጠቂ!
ኀይልሽንም ሁሉ አጠናክሪ!
2አጥፊዎች እነርሱንና
ሀብታቸውን ቢያወድሙም እንኳ
እግዚአብሔር የያዕቆብ ልጆች የሆኑትን
የእስራኤልን ክብር ይመልሳል።
3ወታደሮች ቀያይ ጋሻዎችን አንግበዋል፤
ወታደሮቹ ሐምራዊ ልብስ ለብሰዋል፤
እርሱ ሲያሰልፋቸው የሠረገላዎቹ ብረት ያንጸባርቃል፤
ፈረሰኞቹ በፈረስ ላይ ሆነው ይቊነጠነጣሉ።
4ሠረገሎቹ በከፍተኛ ፍጥነት በመንገዶች ይሽቀዳደማሉ፤
በአደባባዩም ላይ ወዲያና ወዲህ ይጣደፋሉ፤
የሚንቦገቦግ ችቦም ይመስላሉ፤
እንደ መብረቅም ይወረወራሉ።
5እርሱ የጦር ሹማምንቱን ይጠራል፤
እነርሱም እየተደናቀፉ ወደፊት ይመጣሉ፤
የጠላት ወታደሮች እየሮጡ
ወደ ከተማይቱ ቅጽር ይወጣሉ፤
የሚወረወርባቸውንም ፍላጻ
በትልቁ ጋሻቸው ይከላከላሉ።
6በወንዙ በኩል ያሉት የከተማይቱ
ቅጽር በሮች ወለል ብለው ተከፈቱ፤
ቤተ መንግሥቱም በሽብር ተሞላ።
7ነነዌ ተዋረደች፤ ንግሥቲቱ ተማርካ ተወሰደች፤
ሴቶች አገልጋዮችዋ የርግብ ድምፅ የመሰለ የሐዘን ድምፅ ያሰማሉ፤
ደረታቸውንም እየመቱ ያለቅሳሉ።
8ነነዌ ውሃዋ እንደሚፈስ ኩሬ ናት፤
ሕዝብዋም እንደሚፈሰው ውሃ
ከከተማይቱ ወጥቶ ሲሄድ
“ቁሙ! ቁሙ!” የሚለውን ሰው ዞር ብሎ አያይም።
9የከተማይቱ ሀብት መጨረሻ የለውም፤
የከበሩ ድንጋዮቹም የተትረፈረፉ ናቸው፤
ስለዚህ ሄዳችሁ ብሩንና ወርቁን በዝብዛችሁ ውሰዱ።
10ነነዌ ተደመሰሰች፤
ፈራርሳም ወደመች፤
የሰው ልብ በፍርሃት ቀለጠ፤
ጉልበቶችም ተብረከረኩ፤
የሰው ሁሉ ወገብ ተንቀጠቀጠ።
የሰውም ሁሉ ፊት ገረጣ፤
11አንበሶች የሚኖሩበትን፥
የአንበሶች ደቦሎች የሚመገቡበትን፥
ወንድና ሴት አንበሶች ከግልገሎቻቸው ጋር
ያለ ስጋት የሚዝናኑበትን መስክ ትመስል የነበረችው፥
ያቺ ከተማ አሁን የት አለች?
12አንበሳ ለግልገሎቹ የሚበቃቸውን ያኽል ዐድኖ አመጣ፤
ለእንስቲቱ አንበሳም የምትመገበውን ገድሎ አመጣላት፤
ዋሻውን በታደኑ እንስሶች
ጒድጓዱንም በተቦጫጨቀ ሥጋ ሞላ።
13ነነዌ ሆይ! በአንቺ ላይ ተነሥቼአለሁ ይላል የሠራዊት አምላክ፤ ሠረገሎችሽንም አቃጥላለሁ፤ ደቦሎችሽንም ሰይፍ ይበላቸዋል፤ በምድር ላይ በአንቺ ተጠቂ የሚሆን እንዳይኖር አደርጋለሁ፤ የመልእክተኞችሽም ድምፅ ከእንግዲህ ወዲያ አይሰማም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ