ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ወደቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው በመጡ ጊዜ ብዙ ሰዎች በዙሪያቸው ተሰብስበው አዩ፤ የሕግ መምህራንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይከራከሩ ነበር። ሕዝቡም ሁሉ ኢየሱስን ባዩት ጊዜ በመገረም ተደናገጡ፤ ወደ እርሱም ሮጠው እጅ ነሡት። ኢየሱስም “ከእነርሱ ጋር የምትከራከሩት በምን ጉዳይ ነበር?” ሲል ጠየቃቸው። ከሕዝቡም መካከል አንዱ፥ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “መምህር ሆይ፥ ድዳ በሚያደርግ መንፈስ የተያዘውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በሚነሣበትም ጊዜ ይጥለዋል፤ አፉም ዐረፋ እየደፈቀ ጥርሶቹን ያፋጫል፤ ሰውነቱም ደርቆ እንደ በድን ይሆናል፤ ርኩሱንም መንፈስ እንዲያስወጡለት ደቀ መዛሙርትህን ጠይቄአቸው ነበር፤ ነገር ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታምኑ ሰዎች! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? እስቲ ልጁን ወደ እኔ አምጡት!” እነርሱም ልጁን ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩሱም መንፈስ ኢየሱስን ባየ ጊዜ ወዲያው ልጁን ጥሎ አንፈራገጠው፤ ልጁም በመሬት ላይ እየተንከባለለ ዐረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፥ “ይህ በሽታ ከጀመረው ምን ያኽል ጊዜ ነው?” ሲል ጠየቀው። አባትየውም እንዲህ አለ፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው። ሊገድለውም እየፈለገ ብዙ ጊዜ በእሳትና በውሃ ውስጥ ይጥለዋል፤ ግን አንዳች ነገር ማድረግ ብትችል እባክህ እዘንልን! እርዳንም!” ኢየሱስም “ብትችል” ትላለህን? “ለሚያምን ሰው ሁሉ ነገር ይቻላል!” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፥ “ማመንስ አምናለሁ፤ ግን ማመን በሚያቅተኝ ነገር ሁሉ ደግሞ አንተ እርዳኝ!” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም ሕዝቡ እየተራወጡ ሲመጡ አየ፤ ርኩሱንም መንፈስ “አንተ ድዳና ደንቆሮ መንፈስ ከልጁ እንድትወጣ ወደ እርሱም ተመልሰህ እንዳትገባ አዝሃለሁ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ልጁንም በጣም ካንፈራገጠው በኋላ ወጣ፤ ልጁም ልክ እንደ በድን በመሆኑ ብዙዎቹ የሞተ መሰላቸው። ኢየሱስ ግን የልጁን እጅ ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ ቆመ። ኢየሱስም ወደ ቤት በገባ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፦ “ለመሆኑ ይህን ርኩስ መንፈስ እኛ ልናስወጣው ስለምን አልቻልንም?” ብለው ለብቻው ጠየቁት። እርሱም “እንዲህ ዐይነቱ በጸሎትና [በጾም] ካልሆነ በቀር በሌላ በምንም አይወጣም።” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ያንን ስፍራ ትተው በገሊላ በኩል ሄዱ፤ ያለበትን ቦታም ማንም ሰው እንዲያውቅ ኢየሱስ አልፈለገም፤ ይህም የሆነው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከተገደለ በኋላ ግን በሦስተኛው ቀን ይነሣል።” እያለ ያስተምራቸው ስለ ነበር ነው። ደቀ መዛሙርቱ ግን ይህ ነገር አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆም መጡ፤ ኢየሱስ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፦ “በመንገድ ሳላችሁ የተከራከራችሁበት ነገር ምን ነበር?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱ ግን ዝም አሉ፤ ይህም በመንገድ ሳሉ፥ “ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው?” እያሉ ይከራከሩ ስለ ነበረ ነው። እርሱም ከተቀመጠ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን ጠርቶ፥ “መጀመሪያ መሆን የሚፈልግ ማናቸውም ሰው የሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ መሆን አለበት፤” አላቸው። አንድ ሕፃን አምጥቶ በመካከላቸው አቆመው፤ ዐቅፎትም እንዲህ አላቸው፦ “እንደዚህ ካሉት ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ እኔን ሳይሆን፥ የላከኝን ይቀበላል።” ዮሐንስ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያስወጣ አየን፤ ግን ከእኛም ጋር ስላልሆነ ከለከልነው፤” አለው። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “በስሜ ተአምር እያደረገ ወዲያውኑ በእኔ ላይ ክፉ የሚናገር ስለሌለ ተዉት፤ አትከልክሉት፤ እኛን የማይቃወም ሁሉ ከእኛ ጋር ነው፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ አንድ ብርጭቆ ውሃ እንኳ የሚያጠጣቸው ዋጋውን አያጣም፤” አላቸው። “ማንም ሰው በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከትንንሾቹ አንዱን ከሚያስት ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል። ስለዚህ እጅህ ኃጢአት እንድትሠራ ቢያስትህ ቈርጠህ ጣለው! ሁለት እጅ እያለህ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ ጒንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። ገሃነም ትሉ የማይሞትበት፥ እሳቱ የማይጠፋበት ስፍራ ነው። እግርህም ቢያስትህ፥ ቈርጠህ ጣለው፤ ሁለት እግር እያለህ፥ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ፥ አንካሳ ሆነህ፥ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። [ ገሃነም ትሉ የማይሞትበት፥ እሳቱ የማይጠፋበት ስፍራ ነው።] ዐይንህም ቢያስትህ፥ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዐይን እያለህ፥ ወደ ገሃነም ከምትጣል ይልቅ አንድ ዐይና ሆነህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል። ገሃነም ትሉ የማይሞትበት፥ እሳቱም የማይጠፋበት ስፍራ ነው። “መሥዋዕት በጨው እንደሚጠራ እያንዳንዱ ሰው በእሳት መጥራት አለበት። “ጨው መልካም ነው፤ ይሁን እንጂ፥ የጨውነቱን ጣዕም ካጣ በምን ታጣፍጡታላችሁ? “በእናንተም የፍቅር ጨው ጣዕም ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ ተስማምታችሁ በሰላም ኑሩ፤” አለ።
የማርቆስ ወንጌል 9 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 9:14-50
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች