የማርቆስ ወንጌል 6:1-21

የማርቆስ ወንጌል 6:1-21 አማ05

ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ አገሩ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። በሰንበት ቀን በምኲራብ ማስተማር ጀመረ፤ ብዙ ሰዎች በዚያ ተገኝተው ይሰሙት ነበር፤ እነርሱም “ይህ ሰው ይህን ሁሉ ነገር ከየት አገኘው? ምን ዐይነት ጥበብ ተሰጥቶታል? እነዚህንስ ተአምራት የሚያደርገው እንዴት ነው?” እያሉ ይደነቁ ነበር። ቀጥለውም “ለመሆኑ ይህ እንጨት ጠራቢው የማርያም ልጅ አይደለምን? የያዕቆብ፥ የዮሳ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚህ ከእኛ ጋር አይደሉምን?” እያሉ በመናቅ ሳይቀበሉት ቀሩ። ኢየሱስ ግን፥ “ነቢይ በሌሎች ዘንድ ይከበራል፤ በገዛ አገሩ፥ በዘመዶቹና በቤተ ሰቡ መካከል ግን ይናቃል፤” ሲል መለሰላቸው። በዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር ሌላ ተአምር ማድረግ አልቻለም። ሕዝቡ ሳያምኑ በመቅረታቸው እጅግ ተገረመ፤ ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፤ ለመንገዳቸው ከበትር በቀር እንጀራም ሆነ ከረጢት፥ ገንዘብም በመቀነታቸው እንዳይዙ አዘዛቸው። እንዲህም አላቸው፤ “በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀጠባብ እንኳ አትልበሱ፤ በማናቸውም ስፍራ ወደ አንድ ሰው ቤት ስትገቡ፥ ያንን ስፍራ እስክትለቁ ድረስ በዚያው ቈዩ፤ ሰዎች በማይቀበሉአችሁና በማይሰሙአችሁ ቦታ ሁሉ የእግራችሁን አቧራ አራግፉና ከዚያ ወጥታችሁ ሂዱ፤ ይህም ለእነርሱ የማስጠንቀቂያ ምስክር ይሆንባቸዋል።” የተላኩትም ከዚያ ወጥተው፥ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ አስተማሩ። ብዙ አጋንንትንም አስወጡ፤ ብዙ ሰዎችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ። የኢየሱስ ዝና በሁሉም ዘንድ ስለ ታወቀ፥ ንጉሡ ሄሮድስ ስለ እርሱ ሰማ። አንዳንድ ሰዎች፥ “መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት ተነሥቶአል፤ ስለዚህ ይህ ሁሉ ተአምራት በእርሱ ይደረጋል” ይሉ ነበር። ሌሎችም “ኤልያስ ነው፤” ይሉ ነበር፤ የቀሩትም ደግሞ “ከቀድሞዎቹ ነቢያት እንደ አንዱ ነው፤” ይሉ ነበር። ሄሮድስ ግን ይህን ሁሉ ሰምቶ፦ “ይህ እኔ አንገቱን ያስቈረጥኩት ዮሐንስ ነው፤ እነሆ! እርሱ ከሞት ተነሥቶአል፤” አለ። ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮዲያዳን ስለአገባ ዮሐንስን በእርስዋ ምክንያት አስይዞ በወህኒ ቤት አስሮት ነበር። ዮሐንስም የታሰረው፥ ሄሮድስን “የወንድምህን ሚስት ማግባትህ ተገቢ አይደለም!” ብሎት ስለ ነበር ነው። ሄሮዲያዳ በዚህ ተቀይማ ዮሐንስን ልታስገድለው ትፈልግ ነበር፤ ነገር ግን አልቻለችም። ሄሮድስ በመጀመሪያ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ መሆኑን ስለሚያውቅ ይፈራውና ይጠብቀውም ነበር። ሄሮድስ የዮሐንስን ንግግር በሰማ ቊጥር ይታወክ ነበር፤ ይሁን እንጂ በደስታ ይሰማው ነበር። ሄሮድስ የተወለደበትን ቀን ለማክበር ለመንግሥት ባለሥልጣኖች፥ ለጦር ሹማምንትና ለአንዳንድ የታወቁ የገሊላ ነዋሪዎች ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ ይህም ለሄሮዲያዳ ጥሩ አጋጣሚ ሆነላት፤

ተዛማጅ ቪዲዮዎች