የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 12

12
የወይን አትክልት ገበሬዎች ምሳሌ
(ማቴ. 21፥33-46ሉቃ. 20፥9-19)
1ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን በምሳሌ እንዲህ ሲል ይነግራቸው ጀመር፦ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ዙሪያውንም ዐጠረ፤ የወይን መጭመቂያ የሚሆን ጒድጓድ ቆፍሮ አበጀ፤ ለወይኑ ጥበቃ የሚያገለግል ከፍተኛ የግንብ ማማ ሠራ፤ ከዚህም በኋላ የአትክልቱን ቦታ ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። 2ፍሬው በደረሰ ጊዜ፥ ከወይኑ ፍሬ እንዲያመጣለት አገልጋዩን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። 3ገበሬዎቹ ግን አገልጋዩን ይዘው ከደበደቡት በኋላ ባዶ እጁን ሰደዱት። 4እንደገና ባለቤቱ ሌላ አገልጋይ ላከ፤ ገበሬዎቹ ይህንንም በድንጋይ ፈንክተውና አዋርደው ሰደዱት። 5ቀጥሎም ሌላውን ቢልክ ገደሉት፤ እንዲሁም ብዙዎችን ቢልክ፥ አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ ሌሎቹንም ገደሉ። 6አሁን ማድረግ የቀረው የሚወደውን ልጁን መላክ ብቻ ነበር፤ ስለዚህ ‘ልጄንስ ያከብሩት ይሆናል’ ብሎ በማሰብ በመጨረሻ አንድ ልጁን ላከ። 7ነገር ግን ገበሬዎቹ እርስ በርሳቸው ‘ይህማ ወራሹ ነው! ኑ እንግደለው! ርስቱም ለእኛ ይሆናል’ ተባባሉ። 8ስለዚህ ልጁን ይዘው ገደሉት፤ ከወይኑ ተክልም ቦታ ውጪ ጣሉት።
9“እንግዲህ የወይኑ ተክል ጌታ ምን ያደርጋል? ባለቤቱ ራሱ ይመጣል፤ ገበሬዎቹንም ይገድላል፤ የወይኑንም ተክል ለሌሎች ይሰጣል። 10ለመሆኑ፥
‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ
የማእዘን ራስ ሆነ፤ #መዝ. 118፥22-23።
11ይህም የጌታ ሥራ ነው፤
ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው።’ ”
የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍ ቃል አላነበባችሁምን?
12የአይሁድ አለቆች ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ እነርሱን የሚመለከት መሆኑን ስለ ተገነዘቡ ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈርተው ትተውት ሄዱ።
ግብር ስለ መክፈል የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 22፥15-22ሉቃ. 20፥20-26)
13ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስን በንግግሩ ለማጥመድ ወደ እርሱ ተላኩ። 14ቀርበውም እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፥ አንተ እውነተኛ መሆንህን እናውቃለን፤ ሰውንም በመፍራትና በይሉኝታ የምታደርገው ነገር የለም፤ የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት ታስተምራለህ፤ ታዲያ፥ ለሮም ንጉሠ ነገሥት ግብር መክፈል ሕጋዊ ነውን? ወይስ አይደለም? እንገብር ወይስ አንገብር?”
15ኢየሱስም ግብዝነታቸውን ዐውቆ፦ “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስቲ ገንዘቡን አምጡና አሳዩኝ፤” አላቸው።
16እነርሱም ገንዘቡን አመጡለት፤ እርሱም “በዚህ ገንዘብ ላይ ያለው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
እነርሱም “የሮም ንጉሠ ነገሥት ነው፤” አሉት።
17ኢየሱስም “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ፤” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም በመልሱ ተደነቁ።
ስለ ሙታን መነሣት የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 22፥23-33ሉቃ. 20፥27-40)
18“የሙታን መነሣት የለም፤” የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ መጥተው፤ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ #ሐ.ሥ. 23፥8። 19“መምህር ሆይ፥ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ ሴትዮዋን አግብቶ ለሟቹ ዘር ይተካለት፤’ ብሎ ሙሴ ጽፎልናል። #ዘዳ. 25፥5። 20ታዲያ፥ ሰባት ወንድማማች ነበሩ፤ የሁሉም ታላቅ ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ 21ሁለተኛውም ወንድሙ ያቺኑ ሴት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ ሆነ፤ 22በዚህ ሁኔታ ሰባቱም አግብተዋት ዘር ሳይተኩ ሞቱ፤ ከሁሉም በኋላ ደግሞ ሴትዮዋ ሞተች። 23ሰባቱም ወንድማማች በየተራ አግብተዋታልና እንግዲህ ሙታን በሚነሡበት ጊዜ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?”
24ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተ የምትሳሳቱት ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ባለማወቃችሁ አይደለምን? 25ሙታንስ ሲነሡ በሰማይ እንዳሉት መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም። 26ስለ ሙታን መነሣት የሆነ እንደ ሆነ ግን እግዚአብሔር ሙሴን ከቊጥቋጦው እሳት ውስጥ ምን እንደ ተናገረው ከሙሴ መጽሐፍ አላነበባችሁምን? ይኸውም ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤’ ያለው ነው። #ዘፀ. 3፥6። 27ስለዚህ እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ እናንተ ግን እጅግ ትሳሳታላችሁ።”
ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ
(ማቴ. 22፥34-40ሉቃ. 10፥25-28)
28ከሕግ መምህራን አንዱ ክርክራቸውን ይሰማ ነበር፤ ኢየሱስ በመልካም ሁኔታ እንደ መለሰላቸው የሕግ መምህሩ አስተዋለ፤ ወደ ኢየሱስ ቀርቦም “ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። #ሉቃ. 10፥25-28።
29ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ፥ ‘እስራኤል ሆይ! ስማ፤ እግዚአብሔር አምላካችን አንድ አምላክ ነው፤ 30አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ሐሳብህ፥ በፍጹም ኀይልህ ውደድ፤’ የሚል ነው። #ዘዳ. 6፥4-5። 31ይህንንም የሚመስል ሁለተኛው ትእዛዝ፥ ‘ጐረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤’ የሚል ነው። ከነዚህም ከሁለቱ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም።” #ዘሌ. 19፥18።
32የሕግ መምህሩም ኢየሱስን እንዲህ አለው፦ “መምህር ሆይ! ‘እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለህ የተናገርከው ልክ ነው፤ #ዘዳ. 4፥35። 33ስለዚህ ሰው በፍጹም ልቡ፥ [በፍጹም ነፍሱ፥] በፍጹም ሐሳቡ፥ በፍጹም ኀይሉ እግዚአብሔርን መውደድ ይገባዋል፤ እንዲሁም ጐረቤትን እንደ ራሱ አድርጎ መውደድ ይገባዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከማቅረብ ይልቅ እነዚህን ሁለቱን ትእዛዞች መጠበቅ ይበልጣል።” #ሆሴዕ 6፥6።
34ኢየሱስም የሕግ መምህሩ በጥበብና በማስተዋል እንደ መለሰ አይቶ፥ “አንተስ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም፤” አለው።
ከዚህ በኋላ ለኢየሱስ ጥያቄ ሊያቀርብለት የደፈረ ማንም የለም።
ስለ መሲሕ የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 22፥41-46ሉቃ. 20፥41-46)
35ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲያስተምር እንዲህ ብሎ ጠየቀ፤ “የሕግ መምህራን ‘መሲሕ የዳዊት ልጅ ነው፤’ ስለምን ይላሉ? 36ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ፥
‘እግዚአብሔር ለጌታዬ (ለመሲሑ)፥
ጠላቶችህን በእግርህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ
በቀኜ ተቀመጥ፤’ ብሎታል። #መዝ. 110፥1።
37ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ብሎ ከጠራው ታዲያ፥ መሲሕ ለዳዊት እንዴት ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር።
የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን እንደ ተወገዙ
(ማቴ. 23፥1-36ሉቃ. 20፥45-47)
38ኢየሱስ ሲያስተምር እንዲህ አለ፦ “ረጃጅም ልብስ ለብሰው ወዲያና ወዲህ መዞርን፥ በገበያም የክብር ሰላምታ መቀበልን ከሚወዱ ከሕግ መምህራን ተጠንቀቁ፤ 39እነርሱ በምኲራብ የክብር ወንበርን፥ በግብዣም የክብር ስፍራን ለማግኘት ይመርጣሉ። 40ለታይታ በሚያቀርቡት ረጅም ጸሎት እያመካኙ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ቤት ይበዘብዛሉ፤ ስለዚህ እነርሱ የባሰ ፍርድ ይደርስባቸዋል።”
የመበለቲቱ ስጦታ
(ሉቃ. 21፥1-4)
41ኢየሱስ በምጽዋት መቀበያ ሣጥን ፊት ለፊት ተቀምጦ ሳለ ሕዝቡ በሣጥኑ ውስጥ ገንዘብ ሲጨምሩ ያይ ነበር፤ ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ ይጨምሩ ነበር፤ 42አንዲት ድኻ መበለትም መጥታ ሁለት ሳንቲም የሚያኽል የናስ ገንዘብ በዚያ ውስጥ ጨመረች። 43ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ በሣጥኑ ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሰዎች ሁሉ አብልጣ የጨመረች ይህች ድኻ መበለት ናት። 44ሌሎቹ ሁሉ የሰጡት ካላቸው ሀብት የተረፋቸውን ነው፤ እርስዋ ግን ድኻ ሆና ሳለች ምንም ሳታስቀር ያላትን ሁሉ ሰጠች።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ