የማርቆስ ወንጌል 11:12-25

የማርቆስ ወንጌል 11:12-25 አማ05

በማግስቱም ከቢታንያ ሲመለሱ ኢየሱስ ተራበ። ቅጠልዋ የለመለመ የበለስ ዛፍም በሩቅ አይቶ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደ ሆነ በማለት ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ወደ እርስዋ በቀረበ ጊዜ በለስ የሚያፈራበት ወራት ስላልነበረ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ስለዚህ ኢየሱስ የበለስዋን ዛፍ፥ “ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ!” አላት። ይህንንም ሲናገር ደቀ መዛሙርቱ ሰሙ። ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በውስጡ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ያስወጣ ጀመር፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ፤ ማንም ሰው ምንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ እንዲተላለፍ አልፈቀደም። እንዲህም ሲል አስተማራቸው፤ “ ‘ቤቴ ለሕዝብ ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል!’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት።” የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ይህን ሲናገር ሰሙት፤ ሕዝቡም ሁሉ በትምህርቱ ይደነቁ ስለ ነበር ፈሩት፤ ስለዚህ እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ዘዴ ይፈልጉ ነበር። በመሸም ጊዜ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከከተማ ወጡ። በማግስቱ ማለዳ በመንገድ ሲያልፉ የበለሲቱ ዛፍ ከነስርዋ ደርቃ አዩአት። ጴጥሮስም ነገሩ ትዝ ብሎት ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ! እነሆ፥ የረገምሃት ዛፍ ደርቃለች” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ሰው በልቡ ሳይጠራጠር የሚፈልገው ነገር እንደሚፈጸምለት አምኖ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር፤’ ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ በጸሎት ማናቸውንም ነገር ብትለምኑ፥ እንደ ተፈጸመላችሁ አድርጋችሁ እመኑ፤ የምትለምኑትም ሁሉ ይሰጣችኋል። በሰማይ ያለው አባታችሁ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ እናንተም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ ሰው በአንዳች ነገር አስቀይሞአችሁ ከሆነ ይቅርታ አድርጉለት።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች