ትንቢተ ሚክያስ 2
2
ድኾችን የሚጨቊኑ ሰዎች የሚገጥማቸው መጥፎ ዕድል
1ክፉ ሥራ ለመሥራት ለሚያቅዱና በመኝታቸው ሳሉ ተንኰል ለሚያውጠነጥኑ ወዮላቸው! ያን ለማድረግ ሥልጣን ስላላቸው ሌሊቱ ሲነጋ ዕቅዳቸውን በሥራ ላይ ያውሉታል። 2የእርሻ ቦታ ሲፈልጉ የሌላውን ቀምተው ይወስዳሉ፤ ቤትም ሲፈልጉ ነጥቀው ይወስዳሉ፤ የሰውን መብት ረግጠው ሀብቱን ይዘርፋሉ። 3ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ በእናንተ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ፤ ከዚህም ልታመልጡ ፈጽሞ አትችሉም፤ ያ አሠቃቂ ጊዜ ስለሚሆን በትዕቢት መመላለስ አትችሉም። 4በዚያን ቀን ሰዎች ያፌዙባችኋል፤ እንዲህም እያሉ የምፀት ሙሾ ያወርዱላችኋል፦
“እኛ ፈጽሞ ጠፍተናል!
እግዚአብሔር የሕዝባችንን ንብረት ወሰደብን፤
ርስታችንንም ለማራኪዎቻችን አከፋፈለ።”
5ምድሩ ተመልሶ ለእግዚአብሔር ሕዝብ በሚሰጥበት ጊዜ እናንተ ምንም ድርሻ አይኖራችሁም።
6የእነርሱ ነቢያት “ትንቢት አትናገር፤ እንደዚህ ያለው ውርደት የማይደርስብን ስለ ሆነ ስለ ነዚህ ጉዳዮች ትንቢት አትናገር” ይሉኛል። 7ንግግራቸውንም በመቀጠል! “የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ይህ መባል አለበትን? የእግዚአብሔር ትዕግሥት አልቋልን? እነዚህስ የእርሱ ድርጊቶች ናቸውን?” ብለው ይጠይቃሉ፤ ለመሆኑ አካሄዳቸው ቀጥተኛ ለሆነ የእኔ ቃላት መልካም ነገር አያደርጉምን?
8እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ይመልስላቸዋል፦ “በሕዝቤ ላይ በጠላትነት ተነሥታችኋል፤ ከጦርነት ተመልሰው በመተማመን በመካከላችሁ የሚያልፉትን ሰላማዊ ሰዎች ገፈፋችሁ፤ 9በሕዝቤ መካከል ያሉትን ሴቶች ከመልካም ቤት ንብረታቸው አፈናቅላችሁ አሳደዳችሁ፤ ልጆቻቸውንም ከእኔ በረከትና ክብር ዘወትር እንዲለዩ አደረጋችሁ። 10በርኲሰት ምክንያት አሠቃቂ ጥፋት የሚደርስ በመሆኑ በዚህ ማረፍ አይቻልም፤ ስለዚህ ተነሥታችሁ ሂዱ።
11“አንድ ሰው ባዶ ቃላትን በመደርደር ስለ ወይንና ስለ ጠንካራ መጠጥ አስተምራችኋለሁ ቢላችሁ የዚህ ሕዝብ ነቢይ የሚሆነው እርሱ ነው።
12“የእስራኤል ሕዝብ! በጎች በበረት፥ የበግ መንጋም በማሰማሪያ ቦታ እንደሚሰበሰብ በእርግጥ ከእስራኤል ሕዝብ የተረፉትን በአንድነት እሰበስባለሁ፤ ምድሪቱም በሕዝብ የተሞላች ትሆናለች” ይላል እግዚአብሔር።
13መንገዱን በርግዶ በሚከፍትላቸው መሪ አማካይነት በተከፈተው ሰፊ በር ተግተልትለው ይወጣሉ፤ እግዚአብሔርም ንጉሣቸው በፊታቸው እየሄደ ይመራቸዋል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሚክያስ 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997