የማቴዎስ ወንጌል 5:22-42

የማቴዎስ ወንጌል 5:22-42 አማ05

እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በወንድሙ ላይ የሚቈጣ ሁሉ ይፈረድበታል፤ ደግሞም ወንድሙን፥ ‘አንተ የማትረባ!’ ብሎ የሚሳደብ በሸንጎ ይፈረድበታል፤ ‘ደደብ!’ ብሎ የሚሳደብ ሁሉ በገሃነመ እሳት ይፈረድበታል። ስለዚህ አንተ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ፥ ያዘነብህ ወንድም መኖሩን ብታስታውስ፥ መባህን በመሠዊያው ፊት አስቀምጥና፥ ሄደህ በመጀመሪያ ከዚያ ከወንድም ጋር ታረቅ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሰህ መባህን አቅርብ። ባላጋራህ ከሶህ ከእርሱ ጋር ወደ ፍርድ ቤት ስትሄድ በመንገድ ላይ ሳለህ ቶሎ ብለህ ከባላጋራህ ጋር ተስማማ። አለበለዚያ ባላጋራህ ለዳኛ፥ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ ይሰጥህና ወደ ወህኒ ቤት ትገባለህ። በእውነት እልሃለሁ፥ የተፈረደብህን የመጨረሻዋን ሳንቲም ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘አታመንዝር!’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ‘ሴትን ተመልክቶ የተመኛት ሁሉ፥ ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመነዘረ’ እላችኋለሁ። የቀኝ ዐይንህ ለኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ አውጥተህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። ቀኝ እጅህ የኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ ቈርጠህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። “ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍችዋን ማስረጃ ይስጣት” ተብሏል። እኔ ግን “በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በቀር፥ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል” እላችኋለሁ። ደግሞም ለቀደሙ ሰዎች “በሐሰት አትማሉ፤ ነገር ግን መሐላችሁን ለጌታ ፈጽሙ” የተባለውን ሰምታችኋል። እኔ ግን “በፍጹም አትማሉ” እላችኋለሁ። ሰማይ የእግዚአብሔር ዙፋን ስለ ሆነች፥ በሰማይም ቢሆን፥ ምድርም የጌታ እግር ማሳረፊያ ስለ ሆነች በምድርም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ስለ ሆነች በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ ከጸጒርህ አንዲቱን እንኳ ነጭ ወይም ጥቊር ማድረግ ስለማትችል በራስህም ቢሆን አትማል። ስለዚህ ንግግራችሁ “አዎ” ከሆነ “አዎ፥” ወይም “አይደለም” ከሆነ “አይደለም” ይሁን። ከዚህ የተረፈ ቃል ግን ከሰይጣን ነው። “ ‘ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፤ ክፉ የሚያደርግባችሁን ሰው አትበቀሉት። ነገር ግን ቀኝ ጒንጭህን ለሚመታህ፥ ግራ ጒንጭህን አዙርለት። አንድ ሰው ሸሚዝህን ለመውሰድ ፈልጎ ቢከስህ፥ ኮትህንም እንዲወስድ ተውለት። አንድ ሰው ‘ከእኔ ጋር ጥቂት መንገድ ሂድ’ ብሎ ቢያስገድድህ፥ አንተ ደግሞ እጥፍ መንገድ ሂድለት። ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተ መበደር ለሚፈልግ እምቢ አትበለው።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች