የማቴዎስ ወንጌል 27:32-44

የማቴዎስ ወንጌል 27:32-44 አማ05

ከገዢው ግቢ ሲወጡ ሳሉ ስምዖን የተባለውን የቀሬና አገር ሰው አገኙና የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚህ በኋላ ትርጒሙ “የራስ ቅል” ወደ ሆነው ወደ ጎልጎታ ደረሱ። በዚያም ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ለኢየሱስ አቀረቡለት፤ እርሱ ግን ቀመስ አድርጎ ሊጠጣው አልፈለገም። ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ ልብሱን ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። የተከሰሰበትንም ወንጀል የሚያመለክት፥ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው?” የሚል ጽሑፍ በመስቀሉ ራስጌ ላይ አኖሩ። በዚያን ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኝ አንዱን በግራ ሰቀሉ። በአጠገቡ ያልፉ የነበሩትም ሰዎች በንቀት ራሳቸውን እየነቀነቁ፥ “አንተ ቤተ መቅደስን የምታፈርስና በሦስት ቀን የምትሠራው! እስቲ ራስህን አድን! የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ከመስቀል ውረድ!” በማለት ያላግጡበት ነበር። በዚሁም ዓይነት የካህናት አለቆች ከሕግ መምህራንና ከሽማግሌዎች ጋር እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ነበር፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! እርሱ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እንመንበት! እርሱ በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ብሎአል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሚወደው ከሆነ እስቲ አሁን ያድነው!” እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ይሰድቡት ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች