ጴጥሮስ ግን እስከ ካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ተከተለው፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የነገሩን ፍጻሜ ለማየት ከዘበኞች ጋር ተቀመጠ። የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ አባሎች ሁሉ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ለማስፈረድ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር። ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢቀርቡም፥ ሞት የሚያስፈርድበት ምስክርነት አላገኙም፤ በመጨረሻ ሁለት ምስክሮች ቀርበው፥ “ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ’ ብሎአል” ሲሉ ተናገሩ። የካህናት አለቃውም ተነሣና “እነዚህ ሰዎች ለሚመሰክሩብህ ሁሉ ምንም መልስ አትሰጥምን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። የካህናት አለቃውም እንደገና ኢየሱስን “በሕያው እግዚአብሔር ስም ይዤሃለሁ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ መሲሕ እንደ ሆንክ ንገረን!” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ እንዳልከው ነው፤ ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ታዩታላችሁ፤ እንዲሁም በሰማይ ደመና ሆኖ ሲመጣ ታዩታላችሁ እላችኋለሁ።” በዚህ ጊዜ የካህናት አለቃው በብስጭት ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሮአል! እናንተም ስድቡን ሰምታችኋል! ከዚህ የበለጠ ምን ምስክር ያስፈልጋል! ታዲያ፥ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ሲሉ መለሱ። በዚያን ጊዜ ምራቃቸውን ተፉበት፤ ጎሸሙት፤ በጥፊም እየመቱት፥ “መሲሕ ሆይ! ማን ነው የመታህ? እስቲ ትንቢት ተናገር” ይሉት ነበር። ጴጥሮስ ከቤት ውጪ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ በዚያን ጊዜ አንዲት ገረድ ወደ እርሱ ቀርባ “አንተም ከገሊላዊው ኢየሱስ ጋር ነበርክ!” አለችው። እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቅም!” ሲል በሁሉም ፊት ካደ። ሊወጣ ወደ በሩ ሲሄድ አንዲት ሌላ ገረድ አየችውና እዚያ ለነበሩት ሰዎች “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር!” አለች። ጴጥሮስም “ይህን የምትዪውን ሰው አላውቀውም!” ሲል በመማል እንደገና ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እዚያ ቆመው የነበሩ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ጠጋ ብለው፦ “አነጋገርህ ያስታውቃል፤ በእርግጥ አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፦ “እኔ ይህን ሰው አላውቀውም!” እያለ ራሱን መራገምና መማል ጀመረ። ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለው። ወደ ውጭም ወጣና ምርር ብሎ አለቀሰ።
የማቴዎስ ወንጌል 26 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 26:58-75
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos