የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 26:47-68

የማቴዎስ ወንጌል 26:47-68 አማ05

ኢየሱስ ገና ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎች መጡ፤ እነርሱ ከካህናት አለቆችና ከሕዝብ ሽማግሌዎች የተላኩ ነበሩ። ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ ለሰዎቹ “የምትፈልጉት እኔ የምስመው ነውና እርሱን ያዙት” ሲል ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ይሁዳ ወዲያውኑ መጥቶ ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” ብሎ ሳመው። ኢየሱስም “ወዳጄ ሆይ! እንግዲህ የመጣህበትን ጉዳይ ፈጽም” አለው፤ ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ወደ ኢየሱስ ቀረቡና ያዙት። በዚህ ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የካህናት አለቃውን አገልጋይ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልሰህ ክተተው። ለመሆኑ እኔ አባቴን ብለምን እርሱ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ የመላእክት ሠራዊት ሊልክልኝ የማይችል ይመስልሃልን? እንዲህማ ቢሆን ኖሮ ‘መከራ መቀበል አለበት’ የሚለው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እንዴት ይፈጸማል?” በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በዚያ ለተሰበሰቡት ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ወንበዴን እንደምትይዙ እኔን ለመያዝ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? በየቀኑ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ ከእናንተ ጋር ሳለሁ አልያዛችሁኝም ነበር፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው በነቢያት የተጻፈው እንዲፈጸም ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች ወደ ካህናት አለቃው ወደ ቀያፋ ወሰዱት፤ በዚያም የሕግ መምህራንና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ነበር። ጴጥሮስ ግን እስከ ካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ተከተለው፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የነገሩን ፍጻሜ ለማየት ከዘበኞች ጋር ተቀመጠ። የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ አባሎች ሁሉ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ለማስፈረድ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር። ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢቀርቡም፥ ሞት የሚያስፈርድበት ምስክርነት አላገኙም፤ በመጨረሻ ሁለት ምስክሮች ቀርበው፥ “ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ’ ብሎአል” ሲሉ ተናገሩ። የካህናት አለቃውም ተነሣና “እነዚህ ሰዎች ለሚመሰክሩብህ ሁሉ ምንም መልስ አትሰጥምን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። የካህናት አለቃውም እንደገና ኢየሱስን “በሕያው እግዚአብሔር ስም ይዤሃለሁ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ መሲሕ እንደ ሆንክ ንገረን!” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ እንዳልከው ነው፤ ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ታዩታላችሁ፤ እንዲሁም በሰማይ ደመና ሆኖ ሲመጣ ታዩታላችሁ እላችኋለሁ።” በዚህ ጊዜ የካህናት አለቃው በብስጭት ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሮአል! እናንተም ስድቡን ሰምታችኋል! ከዚህ የበለጠ ምን ምስክር ያስፈልጋል! ታዲያ፥ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ሲሉ መለሱ። በዚያን ጊዜ ምራቃቸውን ተፉበት፤ ጎሸሙት፤ በጥፊም እየመቱት፥ “መሲሕ ሆይ! ማን ነው የመታህ? እስቲ ትንቢት ተናገር” ይሉት ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች