ኢየሱስና ተከታዮቹ ወደ ኢየሩሳሌም በቀረቡ ጊዜ በደብረ ዘይት ወደምትገኘው ቤተ ፋጌ ወደምትባለው መንደር ሲደርሱ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ እዚያም አንዲት የታሰረች አህያ ከነውርንጫዋ ወዲያውኑ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢላችሁ ‘ጌታ ስለሚፈልጋቸው ነው’ በሉት። እርሱም አህዮቹን ወዲያውኑ ይልካቸዋል።” ይህም የሆነው በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፦ “የጽዮን ከተማ ለምትባለው ለኢየሩሳሌም፦ ‘እነሆ! ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ በአህያይቱና በውርንጫዋ ላይ ሆኖ ወደ አንቺ ይመጣል!’ ብላችሁ ንገሩአት።” ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ። አህያዋንም ከነውርንጫዋ አመጡለት፤ ልብሳቸውንም በአህዮቹ ጀርባ ላይ አደረጉ፤ ኢየሱስም በዚያ ላይ ተቀመጠ። ከሕዝቡም ብዙዎቹ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ የዛፍ ቅርንጫፍ እየቀጠፉ በመንገድ ላይ ይጐዘጒዙ ነበር። ከሕዝቡም ፊት ለፊት ይሄዱ የነበሩትና ከኋላ ይከተሉ የነበሩት፥ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ ምስጋና ይሁን! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! ሆሳዕና! ምስጋና በአርያም ለእግዚአብሔር ይሁን!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ የከተማው ሰዎች በሙሉ “ይህ ማን ነው?” በማለት ታወኩ። ሕዝቡም “ይህ በገሊላ ምድር ከምትገኝ ከናዝሬት ከተማ የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዚያም የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ሁሉ አስወጣ። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ። “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው። ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሳለ ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡና ፈወሳቸው።
የማቴዎስ ወንጌል 21 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 21:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች