የማቴዎስ ወንጌል 19:1-15

የማቴዎስ ወንጌል 19:1-15 አማ05

ኢየሱስ ይህን ተናግሮ ካበቃ በኋላ ከገሊላ ተነሥቶ፥ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ወደምትገኝ ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፤ ከእነርሱም የታመሙትን እዚያ ፈወሳቸው። በዚያን ጊዜ ፈሪሳውያን ወደ እርሱ ቀረቡና ሊፈትኑት ፈልገው፥ “ሰው ሚስቱን በማንኛውም ምክንያት እንዲፈታ ይፈቀድለታልን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እግዚአብሔር በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን? ደግሞም ‘በዚህ ምክንያት ሰው አባቱንና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር ይዋሓዳል፤ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ’ ስለዚህ እነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አንድ አካል ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። እንግዲህ እግዚአብሔር አጣምሮ አንድ ያደረገውን ሰው አይለየው።” ፈሪሳውያንም “ታዲያ፥ ሙሴ ስለምን ‘ባል ለሚስቱ የፍችዋን የምስክር ወረቀት ሰጥቶ ይፍታት’ ይላል?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ሙሴማ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ የፈቀደላችሁ ልባችሁ ደንድኖ አስቸጋሪዎች በመሆናችሁ ምክንያት ነው፤ በመጀመሪያ ግን እንዲህ አልነበረም። “እኔ ግን፥ ‘አንድ ሰው በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ ሴት ቢያገባ አመነዘረ’ እላችኋለሁ።” ደቀ መዛሙርቱም “የባልና የሚስት ሁኔታ እንዲህ ከሆነ አለማግባት የተሻለ ነው” አሉት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ልዩ ችሎታ ለተሰጣቸው ነው እንጂ ይህ ነገር ለሁሉም አይሆንም። ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፤ ሰው የሰለባቸውም አሉ፤ ለመንግሥተ ሰማይ ሲሉ ራሳቸውን እንደ ስልብ ያደረጉ አሉ፤ ስለዚህ ይህን ሊቀበል የሚችል ይቀበለው።” በዚያን ጊዜ እጁን በላያቸው ላይ ጭኖ እንዲጸልይላቸው ሰዎች ሕፃናትን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ሰዎቹን ገሠጹአቸው። ኢየሱስም፦ “መንግሥተ ሰማይ እንደነዚህ ላሉት ስለ ሆነች ሕፃናትን ተዉአቸው፤ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሉአቸው” አለ። እጁንም ከጫነባቸው በኋላ ከዚያ ስፍራ አልፎ ሄደ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች