የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 13:36-49

የማቴዎስ ወንጌል 13:36-49 አማ05

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሕዝቡን አሰናብቶ ወደ ቤት ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፥ “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ትርጒም አስረዳን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻው ይህ ዓለም ነው፤ መልካሙ ዘር የእግዚአብሔር መንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ የሰይጣን ልጆች ናቸው። እንክርዳዱን የዘራው ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩ የዓለም መጨረሻ ነው፤ ዐጫጆቹ መላእክት ናቸው። ልክ እንክርዳዱ ተነቅሎና በየነዶው ታስሮ እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም የኃጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ከእርሱ መንግሥት ሰብስበው ያወጣሉ፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ጻድቃን ግን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻ ውስጥ የተሸሸገውን ሀብት ትመስላለች። አንድ ሰው ይህን ሀብት ባገኘው ጊዜ መልሶ ደበቀው፤ ከደስታውም ብዛት የተነሣ ሄደና ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛ።” እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ደግሞ መንግሥተ ሰማይ ጥሩ ዕንቊ ለመግዛት የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች፤ ነጋዴውም እጅግ ክቡር የሆነ ዕንቊ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያንን ዕንቊ ገዛ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እንዲሁም መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር የተጣለች መረብን ትመስላለች፤ እርስዋ በየዐይነቱ ዓሣ የምትሰበስብ ናት፤ በሞላች ጊዜ ዓሣ አጥማጆቹ ወደ ባሕሩ ዳር ጐትተው ያወጡአታል፤ ተቀምጠውም መልካም መልካሙን መርጠው በዕቃ ያስቀምጣሉ፤ መጥፎ መጥፎውን ግን ወዲያ ይጥላሉ። በዓለም መጨረሻም እንዲህ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን ይለዩአቸዋል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች