በዚያኑ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው በመሰብሰባቸው በጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ፥ በባሕር ዳር ቆመው ነበር። ከዚያም በኋላ ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ እያለ ይነግራቸው ጀመር፦ “እነሆ! አንድ ገበሬ ለመዝራት ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላው ዘር ብዙ ዐፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ መሬቱም ብዙ ዐፈር ስለሌለበት ጥልቀት አልነበረውም፤ ስለዚህ ዘሩ ወዲያውኑ በቀለ። ይሁን እንጂ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፤ ሥር ስላልነበረውም ደረቀ። ሌላውም ዘር በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል ወደቀ፤ እሾኻማውም ቊጥቋጦ አደገና የዘሩን ቡቃያ አንቆ አስቀረው። ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለና ብዙ ፍሬ አፈራ፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ስለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ሰው የበለጠ ይሰጠዋል፤ ይበዛለታልም፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። እያዩ እንደማያዩ፥ እየሰሙ እንደማይሰሙ ወይም እንደማያስተውሉ ስለ ሆኑ እነሆ፥ እኔ በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። ስለዚህ በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው በእነርሱ ላይ ይፈጸማል፦ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አታደርጉም። የእዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፤ ጆሮአቸው ተደፍኖአል፤ ዐይናቸውም ተጨፍነዋል፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ፥ በዐይናቸው ተመልክተው፥ በጆሮአቸውም ሰምተው፥ በልባቸውም አስተውለው፥ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኳቸው ነበር።’ “የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ የተባረኩ ናቸው። በእውነት እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አላዩም፤ እናንተ የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አልሰሙም።
የማቴዎስ ወንጌል 13 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 13:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos