ደግሞም ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ምን እንደ ሆነ ብታስተውሉ ኖሮ በደል በሌለባቸው ሰዎች ላይ ባልፈረዳችሁም ነበር። እንዲያውም የሰው ልጅ የሰንበትም ጌታ ነው።” ኢየሱስ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ወደ ምኲራባቸው ገባ፤ በዚያም አንድ እጀ ሽባ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስን የሚከሱበትን ምክንያት የፈለጉ አንዳንድ ሰዎች “በሰንበት ቀን በሽተኛን መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው፥ በጉ በሰንበት ቀን በጒድጓድ ውስጥ ቢወድቅበት ስቦ የማያወጣው ማነው? ታዲያ፥ ከበግ ይልቅ ሰው እንዴት አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት ቀን መልካም ነገር ማድረግ የተፈቀደ ነው።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እጀ ሽባውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም በዘረጋው ጊዜ እጁ ድኖ ልክ እንደ ደኅነኛው እጅ ሆነለት። ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጥተው ኢየሱስን እንዴት አድርገው እንደሚገድሉት ተማከሩ። ኢየሱስ ግን ሤራቸውን ዐውቆ ከዚያ ቦታ ገለል አለ፤ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ሄዱ፤ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሳቸው። ሰዎቹን ግን ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። “እነሆ! የመረጥኩት አገልጋዬ ይህ ነው! እርሱ እኔ የምወደውና የምደሰትበት ነው፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ እርሱም ቅን ፍርድን ለሕዝቦች ያውጃል። እርሱ አይከራከርም ወይም አይጮኽም፤ በመንገዶችም ላይ ድምፁን የሚሰማ የለም። የተቀጠቀጠ ሸንበቆ እንኳ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጥዋፍ ክር አያጠፋም፤ ይህንንም የሚያደርገው፥ ቅን ፍርድ ድል እስኪነሣ ድረስ ነው። አሕዛብ በእርሱ ተስፋ ያደርጋሉ።”
የማቴዎስ ወንጌል 12 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 12:7-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች