የማቴዎስ ወንጌል 11:1-30

የማቴዎስ ወንጌል 11:1-30 አማ05

ኢየሱስ እነዚህን ትእዛዞች ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከሰጠ በኋላ ያን ቦታ ትቶ በአቅራቢያው ወደሚገኙት ከተሞች ሊሰብክና ሊያስተምር ሄደ። መጥምቁ ዮሐንስ በወህኒ ቤት ሳለ፥ የክርስቶስን ሥራ በመሰማቱ ሁለት ደቀ መዛሙርት ልኮ፥ “ያ ይመጣል የተባለው መሲሕ አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ብለው ኢየሱስን እንዲጠይቁት አደረገ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሂዱና ያያችሁትንና የሰማችሁትን ሁሉ ለዮሐንስ ንገሩት። እነሆ፥ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ቀጥ ብለው ይሄዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል፤ ስለ እኔ የማይጠራጠር የተባረከ ነው።” የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ፥ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤ “ለመሆኑ ምን ልታዩ ወደ በረሓ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸንበቆ ለማየት ነውን? ደግሞስ ምን ለማየት ወጣችሁ? የተዋበ ልብስ የለበሰውን ሰው ለማየት ነውን? የተዋበ ልብስ የሚለብሱማ በነገሥታት ቤት ይገኛሉ። ታዲያ፥ ስለምን ወጣችሁ? ነቢይ ለማየት ነውን? አዎ፥ እንዲያውም ከነቢይ በጣም የሚበልጠውን ለማየት ነው እላችኋለሁ። እርሱ ‘እነሆ፥ እፊት እፊትህ እየሄደ፥ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ በፊት እልካለሁ’ ተብሎ የተጻፈለት ነው። በእውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዷቸው ሰዎች መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም። ነገር ግን በመንግሥተ ሰማያት በጣም የሚያንሰው ይበልጠዋል። ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማይ በጣም ትገፋለች በብርቱ የሚታገሉም ያገኙአታል። “መላው የነቢያት ትምህርትና በሙሴ እጅ የተሰጠው ሕግ እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋል። እንግዲህ እነርሱ የተናገሩትን ለመቀበል ከፈቀዳችሁ፥ ያ ይመጣል የተባለው ኤልያስ እነሆ፥ ይህ ዮሐንስ ነው። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ! “ነገር ግን የዚህን ዘመን ሰዎች በምን አነጻጽራቸዋለሁ? በአደባባይ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እየጠሩ፥ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ አልጨፈራችሁም! ሙሾ አወረድንላችሁ አላለቀሳችሁም!’ የሚሉትን ልጆች ይመስላሉ። እንዲሁም መጥምቁ ዮሐንስ በመጣ ጊዜ እህል ሳይበላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፥ ‘ይህስ ጋኔን አለበት!’ አሉት፤ የሰው ልጅ ደግሞ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ፥ ‘እነሆ! ይህ መብልና መጠጥ የሚወድ ነው! የቀራጮችና የኃጢአተኞችም ወዳጅ ነው!’ አሉት። ሆኖም የጥበብ ትክክለኛነት ግን በሥራዋ ይረጋገጣል።” ቀጥሎም ኢየሱስ ከሌሎች ከተሞች ይበልጥ ብዙ ተአምራት ያደረገባቸውን ከተሞች፥ ንስሓ ስላልገቡ እንዲህ ሲል ይወቅሳቸው ጀመር፦ “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት፥ በጢሮስና በሲዶና ከተሞች ተደርገው ቢሆን ኖሮ በዚያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የሐዘን ልብስ ለብሰውና ዐመድ በላያቸው ላይ ነስንሰው ገና ዱሮ ንስሓ በገቡ ነበር! ስለዚህ በፍርድ ቀን፥ ከእናንተ ይልቅ በጢሮስና በሲዶና ይኖሩ ለነበሩት ቅጣቱ ይቀልላቸዋል እላችኋለሁ። አንቺም እስከ ሰማይ ከፍ ያልሽው ቅፍርናሆም! ወደ ሲኦል ትወርጂአለሽ! በአንቺ የተደረጉት ተአምራት፥ በሰዶም ተደርገው ቢሆን ኖሮ ያቺ ከተማ ሳትጠፋ፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበር! ስለዚህ በእውነት እልሻለሁ፤ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ቅጣቱ ይቀልላታል!” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ! ይህን ነገር ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለአላዋቂዎች ስለ ገለጥክላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎ! አባት ሆይ! ይህን ለማድረግ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኖአል። አባቴ ሁሉን ነገር ሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ ማንም የለም። እንዲሁም ከወልድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም፤ ማንም ወልድ ካልገለጠለት በቀር አብን ሊያውቅ አይችልም። “እናንተ በጉልበት ሥራ የደከማችሁ! ሸክምም የከበደባችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ! እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህና ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ ነው፤ ሸክሜም ቀላል ነው።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች