የሉቃስ ወንጌል 8:4-18

የሉቃስ ወንጌል 8:4-18 አማ05

ብዙ ሕዝብ ከየከተማው ወደ እርሱ መጥተው በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ተረገጠ፤ ወፎችም በሉት። ሌላውም ዘር በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መሬቱ እርጥበት ስላልነበረው ቡቃያው ደረቀ። ሌላውም ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹ አብሮ አደገና አንቆ አስቀረው። ሌላው ዘር ግን በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለ፤ ቡቃያውም አድጎ እያንዳንዱ መቶ እጥፍ አፈራ።” ቀጥሎም ኢየሱስ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” አለ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “የዚህ ምሳሌ ትርጒም ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ሌሎች ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ እነርሱ እያዩ ልብ እንዳያደርጉ፥ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።” የምሳሌው ትርጒም ይህ ነው፦ “ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ለጊዜው የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። በጭንጫማ መሬት ላይ የወደቀውም ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ሰምተው በደስታ የሚቀበሉትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ የሚያምኑት ለጊዜው ነው፤ ሥር ስለሌላቸውም በፈተና ጊዜ ወዲያውኑ ይክዳሉ። በእሾኽም ቊጥቋጦ መካከል የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ለጊዜው የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ሐሳብና ሀብት፥ የምድራዊ ኑሮ ምቾትም አንቆ ያለ ፍሬ ያስቀራቸዋል። በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ግን በመልካምና በቅን ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁትን ነው፤ እነርሱ በቃሉ ጸንተው ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መብራት አብርቶ እንቅብ የሚደፋበት ወይም በአልጋ ሥር የሚያኖረው ማንም የለም፤ ይልቅስ ወደ ቤት የሚገቡ ሁሉ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል። “እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረ ሳይታወቅ የሚቀር የለም። “ስለዚህ ቃሉን እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፤ ላለው ሰው ተጨምሮ ይሰጠዋል፤ የሌለው ግን አለኝ ብሎ የሚያስበው እንኳ ይወሰድበታል።”