በሰንበት ቀን ኢየሱስ በእርሻ መካከል ሲያልፍ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ የስንዴ እሸት እየቀጠፉ በእጃቸው ማሸትና መብላት ጀመሩ፤ ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ደቀ መዛሙርቱን “በሰንበት ቀን ሊደረግ የማይገባውን ነገር ስለምን ታደርጋላችሁ?” አሉአቸው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እርሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን? እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ከካህናት በቀር ለሌሎች መብላት ያልተፈቀደውን የተቀደሰ የመባ ኅብስት አንሥቶ በላ፤ ከእርሱ ጋር ለነበሩትም ሰዎች ሰጣቸው።” ቀጥሎም ኢየሱስ “የሰው ልጅ ለሰንበትም ጌታዋ ነው፤” አላቸው። በሌላም ሰንበት ቀን ኢየሱስ ወደ ምኲራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ እዚያም ቀኝ እጁ ሽባ የሆነ አንድ ሰው ነበር። የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያንም ኢየሱስን የሚከሱበት ወንጀል ለማግኘት ፈልገው፥ “እስቲ በሰንበት ቀን ይፈውሰው እንደ ሆነ እንይ፤” ብለው ይጠባበቁት ነበር። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እጀ ሽባውን “ተነሥና በመካከል ቁም!” አለው፤ ሽባውም ተነሣና በመካከል ቆመ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “እስቲ ልጠይቃችሁ፤ ለመሆኑ በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነውን? ወይስ ክፉ? ነፍስን ማዳን ነውን ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። ኢየሱስ በዙሪያው ወዳሉት ሰዎች ሁሉ ከተመለከተ በኋላ እጀ ሽባውን፥ “እጅህን ዘርጋ!” አለው። እርሱም እጁን በዘረጋው ጊዜ ዳነለትና እንደ ሌላው እጅ ደኅና ሆነ። የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ግን በጣም ተቈጥተው በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተመካከሩ። አንድ ቀን ኢየሱስ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ፤ እዚያ ሌሊቱን ሙሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ዐደረ። በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠራ፤ ከእነርሱም መካከል ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም ቀጥለው የሚገኙት ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሠየመው፥ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስ፥ ፊልጶስና በርቶሎሜዎስ፥ ማቴዎስና ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና “ቀናተኛ” ተብሎ የሚጠራው ስምዖን፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው አስቆሮታዊው ይሁዳ። ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ከተራራው ወርዶ በሜዳ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ በዚያ ነበሩ፤ እንዲሁም ሊሰሙትና ከበሽታቸው ሊፈወሱ ፈልገው የመጡ፥ እጅግ ብዙ ሕዝብ ነበሩ። እነርሱም የመጡት ከይሁዳ ምድር ከኢየሩሳሌም ከተማ፥ በባሕር አጠገብ ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና ከተሞች ነበር። በርኩሳን መናፍስት ተይዘው ይታወኩ የነበሩት ሰዎችም መጥተው ይፈወሱ ነበር። የማዳን ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን ለመንካት ይፈልጉ ነበር።
የሉቃስ ወንጌል 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 6:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች