የሉቃስ ወንጌል 5:16-32

የሉቃስ ወንጌል 5:16-32 አማ05

እርሱ ግን በየጊዜው ብቻውን ወደ በረሓ እየሄደ ይጸልይ ነበር። አንድ ቀን ኢየሱስ ሲያስተምር ሳለ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን በአጠገቡ ተቀምጠው ነበር፤ እነርሱ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች ሁሉ እንዲሁም ከኢየሩሳሌም ከተማ የመጡ ነበሩ። ኢየሱስ በሽተኞችን የሚፈውስበት የጌታ ኀይል ከእርሱ ጋር ነበረ። እነሆ፥ አንድ ሽባ ሰው በአልጋ የተሸከሙ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጡ፤ ኢየሱስ ወደ ነበረበት ቤትም አግብተው በፊቱ ሊያኖሩት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ሽባውን ወደ ቤት ማግባት አቃታቸው፤ ስለዚህ ወደ ጣራ ላይ ይዘውት ወጡ፤ ጣራውንም ከፍተው በመካከሉ አውርደው ሽባውን ከነአልጋው በኢየሱስ ፊት አኖሩት። ኢየሱስ እምነታቸውን ባየ ጊዜ ሽባውን፥ “አንተ ሰው! ኃጢአትህ ተደምስሶልሃል፤” አለው። የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን “በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ይህ ማነው? ኃጢአትን የሚደመስስ እግዚአብሔር ብቻ ነው እንጂ ሌላ ማነው?” እያሉ ያስቡ ነበር። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “በልባችሁ ስለምን ይህን ታስባላችሁ? ለመሆኑ ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል፥’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ!’ ከማለት የትኛው ይቀላል? ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ለመደምሰስ ሥልጣን እንዳለው ማወቅ አለባችሁ” ብሎ ሽባውን ሰው፦ “አንተ ሰው ተነሥ፤ አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ!” አለው። ሽባውም በሰዎቹ ፊት ወዲያው ተነሣና፥ ተኝቶበት የነበረውን አልጋ ተሸክሞ፥ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ። በዚያም የነበሩ ሰዎች ሁሉ እጅግ ተገርመው፥ በመፍራት፥ “ዛሬ ድንቅ ነገር አየን፤” እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ሲሄድ ሌዊ የተባለውን ቀራጭ በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ አየውና “ተከተለኝ” አለው። ሌዊም ብድግ አለና ሁሉን ነገር ትቶ ተከተለው። ከዚህም በኋላ ሌዊ በቤቱ ለኢየሱስ ክብር ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ በግብዣውም ላይ ብዙ ቀራጮችና ሌሎችም ብዙ ሰዎች ተገኝተው ነበር። ፈሪሳውያንና ወገኖቻቸው የሆኑ የሕግ መምህራን “ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የምትበሉትና የምትጠጡት ስለምንድን ነው?” ብለው በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ አጒረመረሙ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤ እኔ የመጣሁት ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ ለመጥራት ነው እንጂ ጻድቃንን ለመጥራት አይደለም።”