የሉቃስ ወንጌል 22:13-28

የሉቃስ ወንጌል 22:13-28 አማ05

ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ሄደው፥ ሁሉ ነገር ልክ ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙ፤ የፋሲካውንም ራት በዚያ አዘጋጁ። የእራት ሰዓት በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ከሐዋርያት ጋር በማእድ ተቀመጠ። እንዲህም አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን የፋሲካ ራት ለመብላት እጅግ እመኝ ነበር፤ የዚህ ነገር እውነተኛ ምሥጢር በእግዚአብሔር መንግሥት ፍጹም ሆኖ እስኪገለጥ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን የፋሲካ ራት ከቶ አልበላም እላችኋለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ጽዋውን አንሥቶ ከአመሰገነ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እንካችሁ ይህንን ተካፈሉ፤ በእውነት እላችኋለሁ ከአሁን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከዚህ ከወይን ፍሬ የሚገኘውን መጠጥ አልጠጣም።” ቀጥሎም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ከአመሰገነ በኋላ፤ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ፤ ይህ ለእናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ ሰጣቸው። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ ሰጣቸውና እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚፈጸም አዲስ ኪዳን ነው። “ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ እነሆ፥ ከእኔ ጋር በማእድ ነው። የሰው ልጅ ስለ እርሱ አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ይሞታል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት!” እነርሱም “ከእኛ መካከል ይህን ነገር የሚያደርግ የትኛው ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ቀጥሎም እነርሱ፥ “ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው?” እያሉ እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “የዚህ ዓለም ነገሥታት በሕዝቡ ላይ ሥልጣን አላቸው፤ ገዢዎችም የሕዝቡ በጎ አድራጊዎች ይባላሉ፤ እናንተ ግን እንደ እነርሱ ልትሆኑ አይገባም፤ ይልቅስ ከእናንተ መካከል ትልቅ የሆነ እንደ ትንሽ ይሁን፤ አለቃ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን። በማእድ ተቀምጦ ከሚመገበውና ቆሞ ከሚያገለግለው የትኛው ነው ትልቅ? ትልቅ የሚባለው በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደ አገልጋይ ነኝ። እናንተ በመከራዬ ጊዜ ሁሉ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ ቈይታችኋል።