የሉቃስ ወንጌል 20:20-47

የሉቃስ ወንጌል 20:20-47 አማ05

ስለዚህ ኢየሱስን ለመያዝ ምቹ ጊዜ ይጠብቁ ነበር። ለገዥው ሥልጣንና ፍርድ አሳልፈው ለመስጠት የሚያስችላቸውን የወንጀል ቃል ከእርሱ ለማግኘት ይፈልጉ ነበር፤ ስለዚህ ቅን ሰዎች መስለው፥ በንግግሩ የሚያጠምዱትን ሰላዮች ላኩበት። ሰላዮቹም ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ! አንተ የምትናገረውና የምታስተምረው እውነት መሆኑን እናውቃለን፤ የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት ታስተምራለህ እንጂ ለማንም አታዳላም። እስቲ ንገረን! በሕጋችን መሠረት ለሮም ንጉሠ ነገሥት ግብር መክፈል ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?” ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እስቲ ገንዘቡን አሳዩኝ፤ በዚህ ገንዘብ ላይ የተቀረጸው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?” እነርሱም “የሮም ንጉሠ ነገሥት ነው” አሉት። ኢየሱስም “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በሕዝቡ ፊት በንግግሩ ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ ስለዚህ በመልሱ ተደንቀው ዝም አሉ። “ሙታን አይነሡም” የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ! ሙሴ እንዲህ ሲል ጽፎልናል፤ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ ሴትዮዋን አግብቶ ለሟቹ ዘር ያትርፍለት።’ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የሁሉም ታላቅ ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ። ተከታይ ወንድሙም ያቺኑ ሴት አገባት፤ ሦስተኛውም አገባት፤ በዚህ አኳኋን ሰባቱም አግብተዋት ልጆች ሳይወልዱ ሞቱ። ከሁሉም በኋላ ሴትዮዋ ሞተች። ሰባቱም በየተራ አግብተዋታልና ታዲያ ሙታን በሚነሡበት ጊዜ፥ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የዚህ ዓለም ሰዎች ያገባሉ ይጋባሉ፤ ከሙታን ተነሥተው በሚመጣው ዓለም ለመኖር የተገባቸው ሰዎች ግን፥ አያገቡም፤ አይጋቡም። እንደ መላእክት ስለሚሆኑ አይሞቱም፤ ከሞት ስለ ተነሡም የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ስለ ሙታን ትንሣኤ ግን፥ ሙሴ ስለ ቊጥቋጦው እሳት በተናገረው ታሪክ ውስጥ፥ ጌታን ‘የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ’ ብሎ ጠርቶታል። ስለዚህ እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ ሁሉም ለእርሱ በሕይወት ይኖራሉ።” ከሕግ መምህራንም አንዳንዶቹ “መምህር ሆይ! መልካም ተናገርክ!” አሉ። ከዚያም ወዲህ ለኢየሱስ ጥያቄ ሊያቀርብለት የደፈረ ማንም የለም። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “እንዴት መሲሕን የዳዊት ልጅ ነው ይሉታል? ዳዊት እኮ ራሱ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ፦ ‘ጌታ ለጌታዬ ጠላቶችህን በእግርህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው’ ይላል። እንግዲህ ዳዊት ራሱ ጌታ ብሎ ከጠራው ታዲያ፥ መሲሕ ለዳዊት እንዴት ልጁ ሊሆን ይችላል?” ሕዝቡ ሁሉ ሲሰሙት ሳሉ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ረጃጅም ልብስ ለብሰው ወዲያና ወዲህ መዞርን፥ በገበያም የክብር ሰላምታ መቀበልን፥ በምኲራብ የክብር ወንበርን፥ በግብዣም የክብር ስፍራን ከሚወዱ ከሕግ መምህራን ተጠንቀቁ። እነርሱም ለታይታ በሚያቀርቡት ረጅም ጸሎት እያመካኙ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ይበዘብዛሉ፤ ስለዚህ እነርሱን የባሰ ፍርድ ያገኛቸዋል።”