የሉቃስ ወንጌል 18:15-30

የሉቃስ ወንጌል 18:15-30 አማ05

ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባዩ ጊዜ ሰዎቹን ተቈጡአቸው። ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት እንደእነዚህ ላሉት ስለ ሆነች ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሉአቸው። በእውነት እላችኋለሁ! የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን ያልተቀበላት ሰው አይገባባትም።” ከአይሁድ አለቆች አንዱ ኢየሱስን፥ “ቸር መምህር ሆይ፥ የዘለዓለም ሕይወትን ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባኛል?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ቸር የለም። ትእዛዞችን ታውቃለህ፤ እነርሱም ‘አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህን አክብር’ የተባሉት ናቸው።” ሰውየውም “እነዚህን ትእዛዞች ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ” አለው። ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ ሰውየውን፥ “እንግዲያውስ ገና አንድ ነገር ማድረግ ይቀርሃል፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ገንዘቡን ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ የተከማቸ ሀብት ታገኛለህ፤ ከዚያም በኋላ መጥተህ ተከተለኝ” አለው። ሰውየው ግን በጣም ሀብታም ስለ ነበረ፥ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ። ኢየሱስም ሰውየው እንዳዘነ አይቶ፥ እንዲህ አለ፤ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው! ሀብታም ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ፥ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል።” ይህን የሰሙ ሰዎች፦ “ታዲያ በዚህ ሁኔታ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። ኢየሱስ ግን፥ “በሰው ዘንድ የማይቻል ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” አለ። ጴጥሮስም “እነሆ፥ እኛ ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሃል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ብሎ ቤቱን ወይም ሚስቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም ወላጆቹን ወይም ልጆቹን የሚተው ሰው፥ አሁን በዚህ ዓለም በብዙ እጥፍ ይቀበላል፤ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለምን ሕይወት ያገኛል።”