በዚያን ጊዜ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ከብዛታቸውም የተነሣ እርስ በርሳቸው እየተጋፉ ይረጋገጡ ነበር፤ ኢየሱስም በቅድሚያ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር፤ “ከፈሪሳውያን እርሾ ማለትም ከግብዝነታቸው ተጠንቀቁ ማለት ነው። የተሸፈነ ነገር ሳይገለጥ አይቀርም፤ የተሰወረውም ሳይታወቅ አይቀርም። ስለዚህ በጨለማ የተናገራችሁት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፤ በዝግ ቤት ውስጥ በሹክሹክታ በጆሮ የተናገራችሁትም በሰገነት ላይ በይፋ ይነገራል። “ለእናንተ ለወዳጆቼ እንዲህ እላችኋለሁ፤ ሥጋን ከመግደል በቀር ሌላ ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ፤ ነገር ግን ማንን መፍራት እንደሚገባችሁ እነግራችኋለሁ፤ ይኸውም ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን እግዚአብሔርን ነው፤ አዎ፥ እርሱን ብቻ ፍሩ እላችኋለሁ! “አምስት ድንቢጦች በዐሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱ አንድዋ እንኳ በእግዚአብሔር ፊት የተረሳች አይደለችም። የእናንተማ የራሳችሁ ጠጒር እንኳ በሙሉ የተቈጠረ ነው፤ ስለዚህ አትፍሩ! እናንተ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሳያፍር በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ እኔም ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት እመሰክርለታለሁ እላችኋለሁ። በሰው ፊት የሚክደኝን እኔም ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት እክደዋለሁ። “በሰው ልጅ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ቢኖር በደሉ ይቅር ይባልለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ቢኖር ግን በደሉ ይቅር አይባልለትም። “ሰዎች በየምኲራቡ ሲወስዱአችሁ፥ በገዢዎችና በባለሥልጣኖች ፊት ለፍርድ ሲያቀርቡአችሁ ‘ምን እንመልሳለን? እንዴትስ እንናገራለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ። ልትናገሩት የሚገባችሁን በዚያን ሰዓት መንፈስ ቅዱስ ይነግራችኋል።” ከሕዝቡም መካከል አንድ ሰው ኢየሱስን፦ “መምህር ሆይ፥ አባታችን ያወረሰንን ርስት እንዲያካፍለኝ እባክህ ለወንድሜ ንገረው” አለው። ኢየሱስ ግን፥ “አንተ ሰው፥ በእናንተ መካከል ፈራጅ እንድሆንና ርስት እንዳካፍል ማን ሾመኝ?” ሲል መለሰለት። ቀጥሎ ለሁሉም እንዲህ አላቸው፤ “የሰው ሕይወት በሀብቱ ብዛት አይደለም፤ ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ከስስትም ተጠበቁ።” ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “እርሻው ብዙ ሰብል ያስገኘለት አንድ ሀብታም ሰው ነበር፤ እርሱም በሐሳቡ፥ ‘ይህን ሁሉ እህል የማከማችበት ስፍራ ስለሌለኝ ምን ላድርግ?’ እያለ ያሰላስል ነበር። እንዲህም አለ፦ ‘የማደርገው ይህ ነው፤ ጐተራዎቼን ሁሉ አፈርስና ሌሎች ትልልቅ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያ እህሌንና ንብረቴን ሁሉ ሰብስቤ አከማቻለሁ። ከዚህም በኋላ ራሴን፦ እነሆ፥ ለብዙ ዓመት የሚበቃህ ብዙ ሀብት አለህ፤ እንግዲህ ዕረፍት በማድረግ ተዝናና! ብላ! ጠጣ! ደስ ይበልህ! እለዋለሁ’ አለ። እግዚአብሔር ግን ‘አንተ ሞኝ፥ ዛሬ በዚህች ሌሊት ነፍስህ ከአንተ ትወሰዳለች፤ ታዲያ ይህ ያከማቸኸው ሀብት ሁሉ ለማን ይሆናል?’ አለው። “ለራሱ በምድር ላይ ሀብትን የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ፊት ግን ድኻ የሆነ ሰው እንዲሁ ይሆናል።” ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “ስለዚህ ለሕወታችሁ ‘ምን እንበላለን? ለሰውነታችሁም ምን እንለብሳለን?’ በማለት ስለ ኑሮአችሁ አትጨነቁ እላችኋለሁ። ከምግብ ሕይወት፥ ከልብስም ሰውነት ይበልጣል። እስቲ ቊራዎችን ተመልከቱ! እነርሱ አይዘሩም ወይም አያጭዱም፤ የእህል ማከማቻ ቦታ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ይመግባቸዋል፤ እናንተማ ከወፎች የቱን ያኽል ትበልጣላችሁ! ለመሆኑ ከእናንተ መካከል በመጨነቅ በዕድሜው ላይ አንድ ቀን መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ይህን ትንሹን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለምን በሌላው ነገር ትጨነቃላችሁ? የአሸንድዬ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ እስቲ ተመልከቱ፤ እነርሱ በሥራ አይደክሙም፤ አይፈትሉም፤ ይሁን እንጂ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዲቱ ያጌጠ ልብስ አለበሰም። ታዲያ፥ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ በእሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ አስጊጦ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም! “ስለዚህ ‘ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን?’ እያላችሁ በማሰብ አትጨነቁ። ይህን ለማግኘትማ የዚህ ዓለም ሰዎችም ይጨነቁበታል፤ እናንተ ግን ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ የሰማይ አባታችሁ ያውቃል። ይልቅስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይጨመሩላችኋል። “እናንተ እንደ ታናናሽ መንጋ የሆናችሁ ወገኖቼ አትፍሩ፤ የሰማይ አባታችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ ፈቅዶአል። ያላችሁን ሁሉ ሸጣችሁ ገንዘቡን ለድኾች ስጡ፤ የማያረጅ የገንዘብ ቦርሳም አዘጋጅታችሁ ገንዘባችሁን ሌባ በማይደርስበት፥ ብል በማይበላበትና ከቶም በማያልቅበት ቦታ በመንግሥተ ሰማያት አስቀምጡ። ገንዘባችሁ ባለበት ቦታ ልባችሁም በዚያው ይሆናል።”
የሉቃስ ወንጌል 12 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 12:1-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos