አንድ ቀን ኢየሱስ የማያናግር ጋኔን ከአንድ ድዳ ሰው ያስወጣ ነበር፤ ጋኔኑም በወጣ ጊዜ ድዳው ሰው መናገር ጀመረ፤ ሕዝቡም በዚህ ነገር እጅግ ተደነቁ። አንዳንዶች ግን “አጋንንትን የሚያስወጣው የአጋንንት አለቃ በሆነው በብዔልዜቡል ነው፤” አሉ። ሌሎች ደግሞ ሊፈትኑት ፈልገው ከሰማይ አንድ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ መንግሥት ተከፋፍሎ እርስ በርስ የሚለያይ ከሆነ፥ ያ መንግሥት ይጠፋል፤ እንዲሁም አንድ ቤተሰብ እርስ በርሱ ከተለያየ ይወድቃል። ስለዚህ ሰይጣን እርስ በርሱ የሚለያይ ከሆነ የእርሱ መንግሥት እንዴት ጸንቶ መቆም ይችላል? እናንተ ግን ‘እርሱ አጋንንትን የሚያስወጣ በብዔልዜቡል ነው፤’ ትሉኛላችሁ። ታዲያ፥ እኔ አጋንንትን በብዔልዜቡል የማስወጣ ከሆንኩ ልጆቻችሁስ በማን ያስወጡአቸዋል? ስለዚህ የገዛ ልጆቻችሁ እንኳ ይፈርዱባችኋል። እንግዲህ እኔ አጋንንትን በእግዚአብሔር ኀይል የማስወጣ ከሆነ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መምጣትዋን ዕወቁ። “አንድ ኀይለኛ ሰው የጦር መሣሪያ ይዞ ቤቱን የሚጠብቅ ከሆነ ንብረቱ በደንብ ይጠበቅለታል፤ ነገር ግን ከእርሱ የበለጠ ኀይለኛ ሰው መጥቶ ካሸነፈው የተማመነበትን የጦር መሣሪያ ይወስድበታል ንብረቱንም ሁሉ ዘርፎ ያካፍላል። “ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ እኔን ይቃወማል፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ይበትናል። “ርኩስ መንፈስ ከሰው ውስጥ በወጣ ጊዜ የሚያርፍበት ቦታ በመፈለግ ውሃ በሌለበት በደረቅ ምድር ሁሉ ይዞራል፤ የሚያርፍበት ቦታ ካላገኘ ግን ‘ወደወጣሁበት ቤቴ ተመልሼ ልሂድ’ ይላል። ተመልሶ ሲመጣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚህ በኋላ ሄዶ ከእርሱ ይብስ የከፉ ሌሎች ሰባት አጋንንት ይዞ ይመጣል፤ ቀድሞ እርሱ በነበረበት ቤትም ገብተው በዚያ ይኖራሉ፤ የዚያም ሰው የመጨረሻ ሁኔታ ከመጀመሪያው ይልቅ የባሰ ይሆናል።” ኢየሱስ ይህን በሚናገርበት ጊዜ አንዲት ሴት ከሕዝቡ መካከል ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “አንተን ወልዳ ያጠባች እናት የተባረከች ናት፤” አለች። ኢየሱስ ግን “የተባረኩስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው በሥራ ላይ የሚያውሉት ናቸው፤” አላት። ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ መጥተው በተሰበሰቡ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ይህ ትውልድ ክፉ ትውልድ ነው፤ ምልክት ለማየት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። ነቢዩ ዮናስ ለነነዌ ከተማ ሰዎች ምልክት እንደ ነበረ እንዲሁም የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል። የደቡብ ንግሥት በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ በእርሱ ላይ ትፈርዳለች፤ እርስዋ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከዓለም ዳርቻ መጥታለች፤ ነገር ግን እነሆ፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ፤ እንዲሁም የነነዌ ከተማ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው በእርሱ ላይ ይፈርዱበታል፤ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት በሰሙ ጊዜ በኃጢአታቸው ተጸጽተው ንስሓ ገብተዋል፤ ነገር ግን እነሆ፥ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።”
የሉቃስ ወንጌል 11 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 11:14-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች