ሰቈቃወ ኤርምያስ 5
5
ምሕረት ለማግኘት የቀረበ ጸሎት
1እግዚአብሔር ሆይ! በእኛ ላይ የደረሰውን አስብ፤
ውርደታችንንም ተመልከት!
2ርስታችን ለባዕዳን ተሰጠ፤
ቤታችን ሁሉ የባዕዳን መኖሪያ ሆኖአል፤
3አባቶቻችን በጠላት እጅ ተገደሉ፤
ስለዚህ እኛ አባት የሌለን፥ እነሆ እናቶቻችንም ባል አልባ ሆነው ቀርተዋል።
4ለምንጠጣው ውሃ ዋጋ እንከፍልበታለን፤
የማገዶ እንጨት እንኳ በዋጋ መግዛት አለብን።
5ቀንበር እንደተጫኑ እንስሶች በመነዳት እጅግ ደክመናል፤
እንድናርፍም አይፈቀድልንም።
6በቂ ምግብ ለማግኘት ለግብጽና ለአሦር እጃችንን ሰጠን፤
7አባቶቻችን ኃጢአት ሠርተው አለፉ፤
እኛ ግን የእነርሱን ኃጢአት እንሸከማለን።
8ባሪያዎች ይገዙናል፤
ከእጃቸውም ሊያድነን የሚችል የለም።
9በበረሓው ግድያ ስላለ
ምግባችንን ማግኘት የምንችለው
ሕይወታችንን ለአደጋ በማጋለጥ ነው።
10ከራብ ጽናት የተነሣ
ቆዳችን እንደ ምድጃ ጠቈረ።
11ሴቶች በጽዮን ተደፈሩ
በይሁዳ ከተሞችም ደናግል ተዋረዱ።
12መሪዎች እጆቻቸው ታስረው ተንጠለጠሉ፤
ሽማግሌዎችም አልተከበሩም።
13ወጣት ወንዶች ወፍጮ እንዲፈጩ ተገደዱ፤
ወንዶች ልጆች እንጨት በመሸከም ተንገዳገዱ።
14ሽማግሌዎች ከከተማው ሸንጎ ራቁ፤
ወጣቶች ዘፈናቸውን አቆሙ።
15ደስታ ከልባችን ጠፍቶአል፤
በጭፈራችን ቦታ ሐዘን ተተክቶአል።
16ክብራችን ተገፈፈ፤
እኛም ኃጢአት ስለ ሠራን ወዮልን!
17በዚህ ምክንያት ልባችን ታመመ፤
በእነዚህም ነገሮች ምክንያት ዐይኖቻችን ደከሙ።
18የጽዮን ተራራ ባድማ ስለ ሆነች፥
ቀበሮዎች ይመላለሱበታል።
19አንተ ግን እግዚአብሔር ሆይ!
ለዘለዓለም ንጉሥ ነህ፤
ዙፋንህም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል።
20ታዲያ፥ ለምን በፍጹም ዝም አልከን?
ለምንስ ይህን ያኽል ጊዜ ተውከን?
21እግዚአብሔር ሆይ! እንደገና እንቋቋም ዘንድ ወደ አንተ መልሰን!
ሁኔታችንን አድሰህ እንደ ቀድሞ ዘመን አድርገው።
22ይህን ባታደርግ ግን አንተ በፍጹም ትተኸናል፤
ከመጠን በላይም በእኛ ላይ ተቈጥተሃል ማለት ነው።
Currently Selected:
ሰቈቃወ ኤርምያስ 5: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997