ሰቈቃወ ኤርምያስ 3:37-66

ሰቈቃወ ኤርምያስ 3:37-66 አማ05

እግዚአብሔር አስቀድሞ የወሰነው ካልሆነ በትእዛዙ አንድን ነገር ማስደረግ የሚችል ማነው? ደግም ሆነ ክፉ ነገር ተግባራዊ የሚሆነው ልዑል እግዚአብሔር በሚናገረው መሠረት አይደለምን? ሰው በሕይወቱ እያለ በኃጢአት ምክንያት ሲቀጣ የሚያጒረመርመው ለምንድን ነው? አካሄዳችንን መርምረን፤ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ። በሰማይ ወዳለው አምላካችን ልባችንንና እጃችንን እናንሣ። “አምላክ ሆይ! እኛ ኃጢአትና ዐመፅ ሠርተናል፤ አንተም ይቅር አላልከንም። “በቊጣ ተሞልተህ አሳደድከን ያለ ርኅራኄ ገደልከን። ጸሎት አልፎ ሊገባ በማይችልበት ራስህን ጥቅጥቅ ባለ ደመና ሸፈንክ። መኖሪያህን በደመና ሸፈንክ። በሕዝቦች መካከል እንደ ጒድፍና ጥራጊ አደረግኸን። “ጠላቶቻችን ሁሉ አፋቸውን ከፈቱብን ፍርሀትና ውድቀት እንዲሁም ጥፋትና ውድመት በእኛ ላይ ደረሱ። በሕዝቤ ላይ በደረሰው ጥፋት ምክንያት እንባ ከዐይኖቼ እንደ ወንዝ ውሃ ይጐርፋል። “እንባዬ ያለማቋረጥ ይፈስሳል። ይህም የሚሆነው እግዚአብሔር ከሰማይ ወደ ታች ተመልክቶ እስኪያይ ድረስ ነው። በከተማዬ ውስጥ ባሉት ወጣት ሴቶች ላይ የደረሰውን ክፉ ዕድል በማየቴ የመረረ ሐዘን ደረሰብኝ። “ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ ጠላቶቼ እንደ ወፍ አጠመዱኝ። ከነሕይወቴ ጒድጓድ ውስጥ ወርውረው የጒድጓዱን አፍ በድንጋይ ዘጉብኝ። ውሃ ከእራሴ በላይ ሞልቶ ሲፈስ የምሞትበት ጊዜ የተቃረበ መሰለኝ። “እግዚአብሔር ሆይ! በጥልቅ ጒድጓድ ውስጥ ሆኜ፥ ስምህን ጠራሁ። ጆሮህን ወደ እኔ መልስ፤ ለእርዳታም ድረስልኝ” የሚለውን ልመናዬን ሰምተሃል፤ ስለዚህ ዕረፍትን ስጠኝ። በጠራሁህ ጊዜ ወደ እኔ ቀርበህ “አትፍራ!” አልከኝ። “ጌታ ሆይ! የእኔን ጉዳይ ተከታትለህ ሕይወቴን አዳንክ። እግዚአብሔር ሆይ! በእኔ ላይ የደረሰውን በደል ሁሉ አይተሃልና ፍትሕን ስጠኝ። ጠላቶቼ በእኔ ላይ ያላቸውን የበቀል ስሜትና ያቀዱትን ሤራ አይተሃል። “እግዚአብሔር ሆይ! በእኔ ላይ የሰነዘሩትን ስድባቸውንና ያቀዱትንም ሤራ ሰምተሃል። ቀኑን ሙሉ ጠላቶቼ በእኔ ላይ ይንሾካሾካሉ፤ ያጒረመርማሉም። ተቀምጠውም ሆነ ቆመው በቅኔ በእኔ ላይ በአሽሙር የሚሳለቁ መሆናቸውን ተመልከት። “አምላክ ሆይ! ለፈጸሙት ተግባር የሚገባቸውን ዋጋ ስጣቸው። ርግማንህ በእነርሱ ላይ ይሁን! ተስፋ እንዲቈርጡም አድርጋቸው! እግዚአብሔር ሆይ! በቊጣህ አሳዳቸው፤ ከሰማያትም በታች ደምስሳቸው!”