በአምላክ የቊጣ በትር መከራን ያየሁ እኔ ነኝ። ምንም ብርሃን ወደሌለበት ጨለማ መርቶ ወሰደኝ። ቀኑን ሙሉ እኔን ብቻ መላልሶ ቀጣኝ። ሥጋዬንና ቆዳዬን አስረጀ፤ አጥንቶቼንም ሰባበረ። ከበባ አድርጎ ምርር ባለ ሐዘንና ችግር ውስጥ ከተተኝ። ከብዙ ጊዜ በፊት እንደ ሞተ ሰው በጨለማ ውስጥ እንድቀመጥ አስገደደኝ። እንዳላመልጥ ዙሪያዬን አጠረ፤ በከባድ ሰንሰለትም አሰረኝ። ለእርዳታ ጩኸቴን ባሰማም እንኳ አላዳምጥ አለኝ። መንገዴን በተጠረበ ድንጋይ ዘጋ፤ መተላለፊያዬንም አጣመመ። እርሱ ለእኔ እንደሚሸምቅ ድብና እንደ ተደበቀ አንበሳ ነው። ከመንገዴ አውጥቶ ገነጣጠለኝ፤ ብቸኛም አደረገኝ። ቀስቱን ገትሮ ለፍላጾች ዒላማ አደረገኝ። ፍላጻዎቹንም አስፈንጥሮ ወደ ሰውነቴ ጠልቀው እንዲገቡ አደረገ። ለሕዝቤ ሁሉ መሳቂያ ሆንኩ፤ በዘፈናቸውም ቀኑን ሙሉ አፌዙብኝ። ከችግር የተነሣ ሕይወት እንዲመረኝ አደረገ፤ በእሬትም አጠገበኝ። ጥርሶቼ በጠጠር እንዲሰበሩና ፊቴም በዐመድ ላይ እንዲደፋ አደረገ። ሕይወቴ ሰላም እንዲያጣ ተደረገ፤ ደስታም ምን እንደ ሆነ ረሳሁ። ስለዚህ፦ “ክብሬ ተለይቶኛል፤ ከእግዚአብሔር የምጠብቀውም ተስፋ ሁሉ ተቋርጦአል” አልኩ። መከራዬንና ከርታታነቴን ማስታወስ እንደ እሬትና እንደ ሐሞት ሆነብኝ። ስለዚህም ሁኔታ ሁልጊዜ ሳስብ መንፈሴ ይጨነቃል፤ ሆኖም ይህን አንድ ነገር በማስብበት ጊዜ በተስፋ እሞላለሁ። ይኸውም ሳንጠፋ የቀረነው የእግዚአብሔር ምሕረት ከቶ የማያቋርጥና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ ነው። እነርሱ በየማለዳው ይታደሳሉ፤ ስለዚህ የአንተ ታማኝነት ታላቅ ነው። የእኔ አለኝታ እግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ እርሱን ብቻ ተስፋ አደርጋለሁ። እግዚአብሔር በተስፋ ለሚጠባበቁትና እርሱን ለሚፈልጉ መልካም ነው። ሰው የእግዚአብሔርን አዳኝነት ጸጥ ብሎ መጠበቁ መልካም ነው። ሰው በወጣትነቱ መከራን በትዕግሥት ቢቀበል መልካም ነው። እግዚአብሔር መከራውን በሚአመጣበት ጊዜ ጸጥ ብሎ ለብቻው ቢቀመጥ መልካም ነው። እንደገና ተስፋ ሊኖር ስለሚችል ራሱን ዝቅ አድርጎ ያስገዛ። ለሚመታው ጒንጩን ይስጥ፤ ስድብንም ይቀበል። ይህን ሁሉ ቢያደርግ እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይተወውም። ምንም እንኳ ጭንቀት በሰው ላይ እንዲደርስ ቢፈቅድ ከተትረፈረፈ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የተነሣ ይራራል። ይህም የሚሆነው እርሱ በራሱ ፍላጎት በሰው ላይ ችግርንና ሐዘንን ስለማያመጣ ነው። የአገሪቱ እስረኞች ሁሉ በግፍ በሚረገጡበት ጊዜ፥ ልዑል እግዚአብሔር እያየ ሰብአዊ መብት በሚጣስበት ጊዜ፥ የአንድ ሰው ጉዳይ ፍትሕ በሚያጣበት ጊዜ በውኑ ጌታ እነዚህን ነገሮች አያይምን?
ሰቈቃወ ኤርምያስ 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሰቈቃወ ኤርምያስ 3:1-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች