መጽሐፈ ኢዮብ 10
10
1“መኖር ሰልችቶኛል፤
የማሳልፈውን መራራ ሕይወት
በግልጽ አሰማለሁ።
2እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ፦
በእኔ ላይ ያለህን ቅርታ
ግለጥልኝ እንጂ
አትፍረድብኝ!
3ይህን ያኽል ማስጨነቅህ አግባብ ነውን?
አንተ ራስህ የፈጠርከውን ሰው መናቅ ይገባሃልን?
የክፉ ሰዎችስ ሤራ ደስ ያሰኝሃልን?
4የአንተ ዐይን እንደ ሰው ዐይን ነውን?
ወይስ የምታየው እንደ ሰው ነውን?
5የአንተ ቀኖች እንደ ሰው ቀኖች ናቸውን
ወይስ ያንተ ዕድሜ እንደ ሰው ዕድሜ አጭር ነውን?
6የእኔን በደል የምትመለከት፥
ኃጢአቴንም የምትከታተለው፥ ለምንድን ነው?
7በደለኛ አለመሆኔንና ከአንተም እጅ ማንም
ሊያድነኝ እንደማይችል አንተ ታውቃለህ።
8“ቅርጽና መልክ ሰጥተው ያበጁኝ እጆችህ ናቸው፤
ታዲያ፥ አሁን እነዚያ እጆችህ መልሰው ያፈርሱኛልን?
9እንደ ሸክላ ዕቃ ከዐፈር እንደ ሠራኸኝ አስብ፤
ታዲያ፥ አሁን መልሰህ እንደ ትቢያ ልታደቀኝ ነውን?
10እንደ ወተት ፈሳሽ
እንደ ዕርጎም አረጋኸኝ።
11ሰውነቴን በቈዳና በሥጋ ሸፈንከው፥
በአጥንትና በጅማትም አገጣጠምከው።
12ሕይወትንና ዘለዓለማዊ ፍቅርን ሰጥተኸኛል፤
ጥበቃህም መንፈሴን አጸናው።
13ለካስ እነዚህን ነገሮች በልብህ ሰውረኻቸው ኖሮአል፤
ዓላማህም ይህ እንደ ሆነ ዐወቅሁ።
14በደል ብፈጽም አንተ ትመለከታለህ፤
ኃጢአቴንም ሳትቀጣ አታልፈውም።
15ኃጢአት ብሠራ ወዲያው ችግር ውስጥ እወድቃለሁ
ደግ ነገር ብሠራም አልመሰገንም
ተጐሣቊዬ
ኀፍረት ደርሶብኛል።
16ትዕቢት ቢሰማኝ
እንደ አንበሳ አድነህ ትይዘኛለህ፤
እኔንም ለመጒዳት
መላልሰህ ታደርጋለህ።
17በእኔ ላይ የሚመሰክሩ ሰዎች
ዘወትር ታገኛለህ፤
በእኔ ላይ የምታሳየው ቊጣ
እያደገ ይሄዳል፤
እኔን ለማጥቃት ዘወትር አዳዲስ ዕቅዶችን
እንደ ሠራዊት ታሰልፍብኛለህ።
18“አምላክ ሆይ! ስለምን እንድወለድ አደረግኸኝ?
ማንም ሳያየኝ ብሞት መልካም በሆነ ነበር!
19ሳልፈጠር በቀረሁ፥
ከማሕፀንም በቀጥታ ወደ መቃብር ብወሰድ ኖሮ በተሻለኝ ነበር።
20የሕይወቴ ዘመን አጭር አይደለምን?
በዚህች አጭር ዘመን ጥቂት እንድደሰት እባክህ ተወኝ!
21ይኸውም ዳግመኛ ወደማልመለስበት ጭፍግግ ወዳለውና
ድቅድቅ ጨለማ ወደ ሆነው አገር ከመሄዴ በፊት ነው።
22የምሄድበት ስፍራ የጨለማ ጥላና ሁከት የተሞላበት ምድር ነው፤
በዚያም ያለው ብርሃን እንደ ጨለማ ነው።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 10: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997