የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 9:1-27

የዮሐንስ ወንጌል 9:1-27 አማ05

ኢየሱስ በመንገድ ሲያልፍ ዕውር ሆኖ የተወለደ ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ የተወለደው በማን ኃጢአት ነው? በራሱ ኃጢአት ነውን ወይስ በወላጆቹ?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ይህ ሰው ዕውር ሆኖ የተወለደው በእርሱ ወይም በወላጆቹ ኃጢአት ምክንያት አይደለም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው። ቀን ሆኖ ሳለ የላከኝን ሥራ መሥራት አለብኝ፤ ማንም ሰው ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል። በዓለም ላይ ሳለሁ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ።” ይህን ከተናገረ በኋላ በመሬት ላይ እንትፍ አለና በምራቁ ዐፈር ለወሰ፤ በጭቃውም የዕውሩን ዐይኖች ቀባና፥ “ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው። (ሰሊሆም “የተላከ” ማለት ነው።) ስለዚህ ሰውየው ሄዶ ታጠበና እያየ ተመለሰ። ጐረቤቶቹና ቀድሞ ሲለምን ያዩት የነበሩ ሰዎች፥ “ይህ ሰው ያ ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። አንዳንዶች “አዎ፥ እርሱ ነው!” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ “እርሱን ይመስላል እንጂ እርሱ አይደለም!” አሉ። እርሱ ግን “እኔው ነኝ!” አለ። ሰዎቹም “ታዲያ፥ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” አሉት። እርሱም “ኢየሱስ የተባለ ሰው ጭቃ ለውሶ ዐይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም ሄደህ ታጠብ’ አለኝ፤ እኔም ሄጄ ታጠብኩና ለማየት ቻልኩ” ሲል መለሰ። እነርሱም “ሰውየው አሁን የት አለ?” አሉት። እርሱም “የት እንዳለ እኔ አላውቅም” አላቸው። ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ዕውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ኢየሱስ ጭቃ ለውሶ የሰውዬውን ዐይኖች እንዲበሩ ያደረገው በሰንበት ቀን ነበር፤ ፈሪሳውያን “እንዴት ማየት ቻልክ?” ብለው ሰውየውን እንደገና ጠየቁት። እርሱም “ዐይኖቼ ላይ ጭቃ አደረገልኝና ታጠብኩ፤ ከዚያም በኋላ ማየት ቻልኩ” አለ። በዚህ ጊዜ ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፥ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር ከእግዚአብሔር አይደለም” አሉ። ሌሎች ግን “ታዲያ፥ ኃጢአተኛ የሆነ ሰው እነዚህን ተአምራት እንዴት ማድረግ ይችላል?” አሉ። በዚህ ምክንያት በመካከላቸው መለያየት ሆነ። ስለዚህ ዕውር የነበረውን ሰው፥ “አንተስ ዐይኖችህን አበራልኝ ስለምትለው ስለዚያ ሰው ምን ትላለህ?” ሲሉ ደግመው ጠየቁት። እርሱም “ነቢይ ነው!” አለ። ይህ ሰው ዕውር እንደ ነበረና ዐይኖቹም በኋላ እንዴት እንደ ተከፈቱ ወላጆቹን ጠርተው እስከ ጠየቁአቸው ድረስ የአይሁድ ባለ ሥልጣኖች አላመኑም ነበር። ስለዚህ ወላጆቹን፥ “ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? አሁንስ እንዴት ማየት ቻለ?” ሲሉ ጠየቁአቸው። ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ይህ ሰው ልጃችን መሆኑንና ዕውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤ ነገር ግን አሁን እንዴት እንደሚያይና ዐይኖቹንም ማን እንደአበራለት አናውቅም፤ እርሱን ጠይቁት፤ እርሱ በዕድሜው ሙሉ ሰው ስለ ሆነ ስለ ራሱ መናገር ይችላል።” ወላጆቹ ይህን ያሉት ኢየሱስን “መሲሕ ነው” የሚል ሰው ቢኖር የአይሁድ ባለሥልጣኖች ከምኲራብ ሊያስወጡት ተስማምተው ስለ ነበረ እነርሱን በመፍራት ነበር። ስለዚህ ወላጆቹ፥ “እርሱ በዕድሜው ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱን ጠይቁት” አሉ። በዚህ ምክንያት ዕውር የነበረውን ሰው እንደገና ጠርተው “አንተ እውነቱን በመናገር እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት። ዕውር የነበረውም ሰው፥ “እርሱ ኃጢአተኛ መሆኑን እኔ አላውቅም፤ አንድ ነገር ዐውቃለሁ፤ ይኸውም እኔ ዕውር እንደ ነበርኩና አሁን ማየት እንደ ቻልኩ ብቻ ነው” ሲል መለሰ። እነርሱም “ምን አደረገልህ? ዐይኖችህንስ ያዳነው እንዴት ነው?” አሉት። እርሱም “አስቀድሜ ነገርኳችሁ፤ እናንተ ግን መስማት አልፈለጋችሁም፤ ታዲያ፥ ስለምን እንደገና መስማት ትፈልጋላችሁ? እናንተም የእርሱ ደቀ መዛሙርት መሆን ትፈልጋላችሁን?” አላቸው።

Free Reading Plans and Devotionals related to የዮሐንስ ወንጌል 9:1-27