ኢየሱስ በመንገድ ሲያልፍ ዕውር ሆኖ የተወለደ ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ የተወለደው በማን ኃጢአት ነው? በራሱ ኃጢአት ነውን ወይስ በወላጆቹ?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ይህ ሰው ዕውር ሆኖ የተወለደው በእርሱ ወይም በወላጆቹ ኃጢአት ምክንያት አይደለም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው። ቀን ሆኖ ሳለ የላከኝን ሥራ መሥራት አለብኝ፤ ማንም ሰው ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል። በዓለም ላይ ሳለሁ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ።” ይህን ከተናገረ በኋላ በመሬት ላይ እንትፍ አለና በምራቁ ዐፈር ለወሰ፤ በጭቃውም የዕውሩን ዐይኖች ቀባና፥ “ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው። (ሰሊሆም “የተላከ” ማለት ነው።) ስለዚህ ሰውየው ሄዶ ታጠበና እያየ ተመለሰ። ጐረቤቶቹና ቀድሞ ሲለምን ያዩት የነበሩ ሰዎች፥ “ይህ ሰው ያ ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። አንዳንዶች “አዎ፥ እርሱ ነው!” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ “እርሱን ይመስላል እንጂ እርሱ አይደለም!” አሉ። እርሱ ግን “እኔው ነኝ!” አለ። ሰዎቹም “ታዲያ፥ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” አሉት። እርሱም “ኢየሱስ የተባለ ሰው ጭቃ ለውሶ ዐይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም ሄደህ ታጠብ’ አለኝ፤ እኔም ሄጄ ታጠብኩና ለማየት ቻልኩ” ሲል መለሰ።
የዮሐንስ ወንጌል 9 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 9:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos