ከባሕሩ ማዶ ባገኙትም ጊዜ፥ “መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ተአምራት ስላያችሁ አይደለም። ለሚጠፋ ምግብ አትሥሩ፤ ይልቅስ እግዚአብሔር አብ የማረጋገጫ ማኅተም ስለ አተመው የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ፥ የዘለዓለም ሕይወት ለሚሆነው ምግብ ሥሩ።” ሰዎቹም “ታዲያ፥ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ ይገባናል?” አሉት። ኢየሱስም “የእግዚአብሔር ሥራማ እግዚአብሔር በላከው ማመን ነው” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ “እኛ አይተን በአንተ እንድናምን ምን ተአምር ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ‘እንዲበሉ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ አባቶቻችን በበረሓ መና በልተዋል።” በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ከሰማይ የወረደውን እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ እውነተኛውን እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው፤ የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድና ለዓለም ሕይወትን የሚሰጥ ነው።” ስለዚህ ሰዎቹ “ጌታ ሆይ! ይህን ዐይነት እንጀራ ዘወትር ስጠን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ፈጽሞ አይራብም፤ በእኔ የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም፤ እናንተ ግን አይታችሁኛል፤ ግን በእኔ አላመናችሁም እላችኋለሁ። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ፈጽሞ ወደ ውጪ አላባርረውም። እኔ ከሰማይ የወረድኩት የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ እንጂ የራሴን ፈቃድ ለማድረግ አይደለም። የላከኝ ፈቃድ፥ ከሰጠኝ ሁሉ አንድ እንኳ ሳላጠፋ በመጨረሻው ቀን ከሞት እንዳስነሣቸው ነው። አዎ! የአባቴ ፈቃድ ወልድን የሚያይና በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲያገኝ ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሣዋለሁ።” ስለዚህ ኢየሱስ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” በማለቱ አይሁድ በእርሱ ላይ አጒረመረሙ፤ እንዲህም አሉ፦ “ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? አባቱንና እናቱንስ እናውቃቸው የለምን? ታዲያ፥ አሁን እርሱ እንዴት ‘ከሰማይ ወረድኩ’ ይላል?” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ አታጒረምርሙ፤ የላከኝ አብ የሳበው ካልሆነ በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚችል ማንም የለም፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም በመጨረሻ ቀን ከሞት አስነሣዋለሁ። በነቢያት መጻሕፍት ‘ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፎአል፤ ስለዚህ ከአብ ሰምቶ የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። ይህም ማለት አብን ያየው ሰው አለ ማለት አይደለም፤ አብን ያየው ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣው እርሱ ብቻ ነው። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ (በእኔ) የሚያምን ሰው የዘለዓለም ሕይወት አለው። እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ፤ አባቶቻችሁ በበረሓ መና በሉ፤ ነገር ግን ሞቱ፤ ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው፤ ይህን እንጀራ የሚበላ በፍጹም አይሞትም። ከሰማይ የወረደው ሕይወትን የሚሰጥ እንጀራ እኔ ነኝ፤ ከዚህ እንጀራ የሚበላ ሁሉ ለዘለዓለም ይኖራል፤ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን እኔ የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” በዚህ ጊዜ አይሁድ “ይህ ሰው ሥጋውን እንድንበላ እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” በማለት እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ፥ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላና ደሜንም የሚጠጣ ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል፥ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነው። ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝና እኔም በእርሱ ሕያው እንደ ሆንኩ እንዲሁም ሥጋዬን የሚበላ ሁሉ በእኔ ሕያው ይሆናል። እንግዲህ ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው፤ እርሱም አባቶቻችሁ እንደ በሉት ዐይነት አይደለም፤ ያን እንጀራ የበሉ ሞተዋል፤ ይህን እንጀራ የሚበሉ ግን ዘለዓለም ይኖራሉ።” ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም በምኲራብ በሚያስተምርበት ጊዜ ነበር። ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ይህን በሰሙ ጊዜ፥ “ይህ አነጋገር ከባድ ነው፤ ማን ሊቀበለው ይችላል?” አሉ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንዳጒረመረሙ በመንፈሱ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ይህ ነገር ያሰናክላችኋልን? የሰው ልጅ ወደነበረበት ተመልሶ ሲወጣ ስታዩ ምን ልትሉ ነው? ሕይወትን የሚሰጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሰው ኀይል ግን ለምንም አይጠቅምም፤ እኔ ለእናንተ የተናገርኩት ቃል መንፈስ ነው፤ ሕይወትም ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ መካከል አንዳንዶች የማያምኑ አሉ፤” ኢየሱስ ይህን የተናገረው ከመጀመሪያ አንሥቶ የማያምኑ እነማን እንደ ነበሩና አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው። ቀጥሎም ኢየሱስ “ከአብ የተፈቀደለት ካልሆነ በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚችል የለም ያልኳችሁ ስለዚህ ነው” አለ። በዚህም ምክንያት ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ኢየሱስን መከተል ተዉ። ስለዚህ ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት፥ “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁን?” አላቸው። በዚህ ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ! ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል አለህ። እኛስ አምነናል፤ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ አንተ እንደ ሆንክም ዐውቀናል።” ኢየሱስም “እናንተን ዐሥራ ሁለታችሁን መርጬአችሁ የለምን? ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ዲያብሎስ ነው” አላቸው። ይህንንም ያለው ስለ ስምዖን ልጅ ስለ አስቆሮታዊው ይሁዳ ነበር፤ ይሁዳ ምንም እንኳ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ቢሆን ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ስለ ነበር ነው።
የዮሐንስ ወንጌል 6 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 6:25-71
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos