ስለዚህ ከማእድ ተነሣና ልብሱን አስቀመጠ፤ ማበሻ ጨርቅም አንሥቶ በወገቡ ታጠቀ። ከዚህ በኋላ በመታጠቢያ ዕቃ ውሃ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብ ጀመረ፤ በታጠቀውም ማበሻ ጨርቅ እግራቸውን አበሰ። ኢየሱስ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ በመጣ ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ፥ “ጌታ ሆይ! አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም “አንተ የእኔን እግር ከቶ አታጥብም!” አለው። ኢየሱስም “እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ድርሻ የለህም” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! እንዲህስ ከሆነ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንም፥ ራሴንም እጠበኝ!” አለው። ኢየሱስም “ሰውነቱን የታጠበ ሁለመናውም ንጹሕ በመሆኑ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፤ እናንተም ንጹሖች ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም ንጹሖች አይደላችሁም” አለው። ኢየሱስ “ሁላችሁም ንጹሖች አይደላችሁም” ያለው አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው። እግራቸውን ካጠበ በኋላ ልብሱን ለበሰና ወደ ቦታው ተመልሶ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ምን እንዳደረግሁላችሁ አስተዋላችሁን? እናንተ ‘መምህርና ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ እኔ መምህርና ጌታ ስለ ሆንኩ ያላችሁት ትክክል ነው። እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን መተጣጠብ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁት እናንተም እንድታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ።
የዮሐንስ ወንጌል 13 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 13:4-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos