የዮሐንስ ወንጌል 13:1-20

የዮሐንስ ወንጌል 13:1-20 አማ05

እነሆ፥ ጊዜው ከአይሁድ ፋሲካ በዓል በፊት ነበር፤ ኢየሱስ ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት መድረሱን ዐወቀ። በዚህ በዓለም ያሉትን የራሱን ወገኖች ወዶአቸው ነበር፤ እስከ መጨረሻም ወደዳቸው። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ራት ይበሉ ነበር፤ የስምዖን ልጅ አስቆሮታዊው ይሁዳ ግን ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ዲያብሎስ በልቡ ክፉ ሐሳብ አሳደረበት። አብ ሥልጣንን ሁሉ እንደ ሰጠውና ከእግዚአብሔር ወጥቶ እንደመጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም እንደሚሄድ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ከማእድ ተነሣና ልብሱን አስቀመጠ፤ ማበሻ ጨርቅም አንሥቶ በወገቡ ታጠቀ። ከዚህ በኋላ በመታጠቢያ ዕቃ ውሃ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብ ጀመረ፤ በታጠቀውም ማበሻ ጨርቅ እግራቸውን አበሰ። ኢየሱስ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ በመጣ ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ፥ “ጌታ ሆይ! አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም “አንተ የእኔን እግር ከቶ አታጥብም!” አለው። ኢየሱስም “እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ድርሻ የለህም” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! እንዲህስ ከሆነ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንም፥ ራሴንም እጠበኝ!” አለው። ኢየሱስም “ሰውነቱን የታጠበ ሁለመናውም ንጹሕ በመሆኑ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፤ እናንተም ንጹሖች ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም ንጹሖች አይደላችሁም” አለው። ኢየሱስ “ሁላችሁም ንጹሖች አይደላችሁም” ያለው አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው። እግራቸውን ካጠበ በኋላ ልብሱን ለበሰና ወደ ቦታው ተመልሶ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ምን እንዳደረግሁላችሁ አስተዋላችሁን? እናንተ ‘መምህርና ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ እኔ መምህርና ጌታ ስለ ሆንኩ ያላችሁት ትክክል ነው። እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን መተጣጠብ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁት እናንተም እንድታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላኪው አይበልጥም። ይህን ነገር ብታውቁና በሥራ ላይ ብታውሉት የተባረካችሁ ናችሁ። ይህን የምናገረው ስለ ሁላችሁም አይደለም፤ እኔ የመረጥኳችሁን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ‘እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ በጠላትነት ተነሣብኝ’ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል መፈጸም አለበት። ይህ ከመሆኑ በፊት አሁን አስቀድሜ የምነግራችሁ፤ ከተፈጸመ በኋላ፥ በእኔ ማንነት እንድታምኑ ነው። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።”