የዮሐንስ ወንጌል 10
10
የኢየሱስ መልካም እረኛነት
1ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች በረት በበር ሳይሆን በሌላ በኩል የሚገባ ሰው ሌባና ወንበዴ ነው። 2በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። 3ለእርሱ የበር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹ ድምፁን ይሰማሉ፤ እርሱም የራሱን በጎች በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ እየመራም ወደ ውጪ ያወጣቸዋል። 4የራሱን በጎች ካስወጣ በኋላም እፊት እፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። 5የሌላውን ድምፅ ግን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉም።”
6ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የተናገረውን አላስተዋሉም።
7ስለዚህ ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ፤ 8ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ በጎቹ ግን አልሰሙአቸውም። 9በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣል፤ መሰማሪያም ያገኛል። 10ሌባው የሚመጣው ለመስረቅ፥ ለማረድና ለማጥፋት ብቻ ነው፤ እኔ ግን የመጣሁት ሕይወት እንዲያገኙና የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲኖራቸው ነው።
11“መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። 12በጎቹ የራሱ ያልሆኑ ቅጥረኛ እንጂ እውነተኛ ያልሆነ እረኛ ግን ተኲላ ሲመጣ በሚያይበት ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኲላውም በጎቹን ነጥቆ ይበታትናቸዋል። 13እረኛው የሚሸሸውም ቅጥረኛ ስለ ሆነና ለበጎቹም ስለማያስብ ነው። 14መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ እኔ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ በጎቼም እኔን ያውቁኛል። #ማቴ. 11፥27፤ ሉቃ. 22፥33፤ ዘሌ. 24፥16። 15እኔ እነርሱን የማውቃቸው አብ እኔን እንደሚያውቀኝና እኔም አብን እንደማውቀው ዐይነት ነው፤ እኔ ስለ በጎቼ ሕይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁ። 16በዚህ መንጋ ውስጥ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት ይገባኛል፤ እነርሱ ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ ይሆናል።
17“እንደገና መልሼ እወስዳት ዘንድ ሕይወቴን የምሰጥ ስለ ሆንኩ አብ እኔን ይወደኛል። 18ሕይወቴን በፈቃዴ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ የሚወስዳት ማንም የለም፤ ሕይወቴን ለመስጠትና መልሼም ለመውሰድ ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልኩት ከአባቴ ነው።”
19ከዚህ ንግግር የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደገና መለያየት ሆነ። 20ከእነርሱም ብዙዎቹ፥ “እርሱ ጋኔን አለበት፤ አብዶአል፤ ስለምን ትሰሙታላችሁ?” አሉ።
21ሌሎች “ይህ ንግግር ጋኔን ካለበት ሰው አንደበት የሚወጣ አይደለም፤ ጋኔን የዕውርን ዐይን ማብራት ይችላልን?” አሉ።
የአይሁድ አለማመን
22በኢየሩሳሌም የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል የሚከበርበት ጊዜ ደረሰ፤ ወቅቱም ክረምት ነበር፤ 23ኢየሱስ በቤተ መቅደስ በሰሎሞን መተላለፊያ ይመላለስ ነበር። 24በዚያን ጊዜ አይሁድ በዙሪያው ተሰብስበው፥ “እስከ መቼ በጥርጣሬ ታቈየናለህ? አንተ መሲሕ እንደ ሆንክ በግልጥ ንገረን” አሉት።
25ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የምሠራው ሥራ ስለ እኔ ይመሰክራል። 26እናንተ ግን ከበጎቼ መንጋ ስላልሆናችሁ አታምኑም። 27በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል። 28እኔ የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ስለዚህ ከቶ አይጠፉም፤ ከእኔ እጅ ማንም ነጥቆ አይወስዳቸውም። 29እነርሱን ለእኔ የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል። ከአባቴ እጅ እነርሱን ነጥቆ መውሰድ የሚችል ማንም የለም። 30እኔና አብ አንድ ነን።”
31በዚህ ጊዜ አይሁድ ኢየሱስን ለመውገር እንደገና ድንጋይ አነሡ። 32ኢየሱስም “ከአብ ዘንድ ብዙ መልካም ሥራዎችን አሳየኋችሁ፤ ታዲያ፥ የምትወግሩኝ ከእነዚህ ስለየትኛው ሥራ ነው?” አላቸው።
33እነርሱም “እኛ የምንወግርህ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ስለ መናገርህ ነው እንጂ ስለ መልካም ሥራህ አይደለም፤ ይኸውም አንተ ሰው ሆነህ ሳለ፥ ራስህን አምላክ ስላደረግህ ነው” ሲሉ መለሱለት።
34ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “በሕጋችሁስ ‘እናንተ አማልክት ናችሁ አልኩ’ የሚል ተጽፎ የለምን? #መዝ. 82፥6። 35እንግዲህ ቅዱስ መጽሐፍን መሻር አይቻልም፤ የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ቅዱስ መጽሐፍ አማልክት ብሎ ከጠራቸው 36ታዲያ፥ አብ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ስለ አለ ስለምን ‘በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ትናገራለህ’ ትሉታላችሁ? 37እኔ የአባቴን ሥራ የማልሠራ ከሆንኩ አትመኑኝ። 38የአባቴን ሥራ የምሠራ ከሆንኩ ግን በእኔ እንኳ ባታምኑ በሥራዬ እመኑ፤ በዚህ ዐይነት አብ በእኔ እንደ ሆነና እኔም በአብ እንደ ሆንኩ በሚገባ ታውቃላችሁ።”
39እነርሱም እንደገና ሊይዙት ፈለጉ፤ እርሱ ግን ከእጃቸው አምልጦ ሄደ።
40እንደገናም ኢየሱስ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ዮሐንስ መጀመሪያ ያጠምቅበት ወደነበረው ስፍራ ሄደ፤ በዚያም ቈየ። #ዮሐ. 1፥28። 41ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ መጥተው “ዮሐንስ ምንም ተአምር አላደረገም፤ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ” አሉ። 42እዚያም ብዙ ሰዎች በእርሱ አመኑ።
Currently Selected:
የዮሐንስ ወንጌል 10: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997