የዮሐንስ ወንጌል 1:1-11

የዮሐንስ ወንጌል 1:1-11 አማ05

ቃል በመጀመሪያ ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበረ። እርሱ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጠረ፤ ከተፈጠረው ሁሉ፥ አንድም ነገር ያለ እርሱ የተፈጠረ የለም። በእርሱ ሕይወት ነበረ፤ ይህም ሕይወት የሰዎች ብርሃን ነበረ። ብርሃን በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም ብርሃንን አያሸንፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ በእርሱ ምስክርነት ሰው ሁሉ እንዲያምን ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ መጣ። እርሱ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። እርሱም በዓለም ነበረ፤ ዓለምም የተፈጠረው በእርሱ ነው፤ ዓለም ግን አላወቀውም። ወደ ወገኖቹ መጣ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም።