ትንቢተ ኤርምያስ 7
7
ኤርምያስ በቤተ መቅደስ እንዳስተማረ
1-3እግዚአብሔር የይሁዳ ሕዝብ ወደሚሰግዱበት ወደ ቤተ መቅደሱ የቅጽር በር ላከኝ፤ በዚያ ቆሜ እንድነግራቸው ያዘዘኝ ቃል ይህ ነው፦ “የአኗኗራችሁንና የተግባራችሁን ሁኔታ ለውጡ፤ እኔም በዚህች ምድር እንድትኖሩ እፈቅድላችኋለሁ፤ 4‘ይህ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው! ይህ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው፤ ይህ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው! እኛም በሰላም እንኖራለን!’ በምትሉት ከንቱ ቃላችሁ አትታመኑ።
5“ይልቅስ የአኗኗራችሁንና የተግባራችሁን ሁኔታ ለውጡ፤ እርስ በርሳችሁ ቅንነት በሞላበት ፍቅር ተሳስራችሁ ኑሩ፤ 6መጻተኞችን፥ እናትና አባት የሞቱባቸውን ልጆችና፥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በመጨቈን አትበዝብዙ፤ በዚህች ምድር የሚኖሩ ንጹሓን የሆኑ ሰዎችን በግፍ አትግደሉ፤ እንዳትጠፉም ለሐሰተኞች አማልክት አትስገዱ። 7በዚህ ዐይነት ለውጥ የምታሳዩ ከሆነ ለቀድሞ አባቶቻችሁ ለዘለዓለም ርስት አድርጌ በሰጠኋቸው በዚህች ምድር እንድትኖሩ እፈቅድላችኋለሁ።
8“ተመልከቱ! እናንተ እኮ በሚያታልሉ ከንቱ ቃላት ትተማመናላችሁ፤ 9ከዚህም የተነሣ ትሰርቃላችሁ፤ ትገድላላችሁ፤ ታመነዝራላችሁ፤ ምላችሁም በሐሰት ትመሰክራላችሁ፤ ለባዓል መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ከዚህ በፊት የማታውቁአቸውን አማልክት ታመልካላችሁ። 10እኔ የምጠላውን ይህን ሁሉ ነገር ከፈጸማችሁ በኋላ ወደ ቤተ መቅደሴ መጥታችሁ በፊቴ በመቆም ‘እኛ ከጥፋት ድነናል!’ ትላላችሁ። 11ቤተ መቅደሴ የሌቦች መደበቂያ ዋሻ መሰላችሁን? የምታደርጉትን ሁሉ እነሆ እኔ ራሴ አይቼአለሁ፤ #ማቴ. 21፥13፤ ማር. 11፥17፤ ሉቃ. 19፥46። 12እኔ እንድመለክበት በመጀመሪያ መርጬው ወደነበረው ቦታ ወደ ሴሎ ሂዱ፤ እዚያም ምን እንዳደረግሁት ተመልከቱ፤ በሕዝቤ በእስራኤል ኃጢአት ምክንያት ሴሎን ደመሰስኩት። 13እናንተ ይህን ሁሉ በደል ፈጸማችሁ፤ ደጋግሜ ብነግራችሁም አናዳምጥም ብላችኋል፤ በጠራኋችሁም ጊዜ መልስ አልሰጣችሁኝም። 14ስለዚህ በሴሎ ያደረግኹትን በዚህ በምትታመኑበት በቤተ መቅደሴ አደርጋለሁ፤ ለቀድሞ አባቶቻችሁና ለእናንተ በሰጠሁት በዚህ ቦታ በሴሎ ያደረግኹትን ደግሜ አደርጋለሁ። #ኢያሱ 18፥1፤ መዝ. 78፥60፤ ኤር. 26፥6። 15ወንድሞቻችሁ የሆኑትን የእስራኤልን ሕዝብ እንዳሳደድኩ፥ እናንተንም ከፊቴ አሳድዳችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
የሕዝብ አለመታዘዝ
16እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ኤርምያስ ሆይ! ስለ ነዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ስለ እነርሱ በመጸለይም አትጩኽ፤ ስለማልማለድህ ስለ እነርሱ ልትማልደኝ አያስፈልግም፤ 17ይልቅስ በኢየሩሳሌም መንገዶችና በይሁዳ ከተሞች የሚያደርጉትን ሁሉ አትመለከትምን? 18ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ፤ አባቶች እሳት ያቀጣጥላሉ፤ ሴቶች ‘የሰማይ ንግሥት’ ለተባለችው ጣዖት ኅብስት ለመጋገር ሊጥ ያቦካሉ፤ እኔንም ለማስቈጣት ለሌሎች አማልክት የወይን ጠጅ መባ ያቀርባሉ። #ኤር. 44፥7-19። 19በዚህ እኔን የሚያስቈጡ ይመስላቸዋልን? ይልቅስ ራሳቸውን ይጐዳሉ፤ ኀፍረትንም በራሳቸው ላይ ያመጣሉ፤ 20ስለዚህ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሴ በተሠራበት በዚህ ቦታ ላይ ብርቱ ቊጣዬን አፈሳለሁ፤ በሰዎችና በእንስሶች ላይ፥ በዛፎችና በሰብልም ሁሉ ላይ ሳይቀር አፈሰዋለሁ፤ ቊጣዬ ማንም ሊያጠፋው እንደማይችል እሳት ይሆናል።
21“እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ እላለሁ፦ ‘በመሠዊያችሁ ላይ የምታቀርቡትን የሚቃጠለውንም ሆነ ሌላውን መሥዋዕታችሁን ሰብስባችሁ ሥጋውን ለራሳችሁ ብሉት።’ 22የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብጽ ባወጣኋቸውም ጊዜ ስለሚቃጠልም ሆነ ስለ ሌላው ዐይነት መሥዋዕት ምንም ትእዛዝ አልሰጠኋቸውም፤ 23ነገር ግን እኔ አምላካቸው ስሆን እነርሱም ሕዝቤ ይሆኑ ዘንድ ለእኔ መታዘዝ እንደሚገባቸው ብቻ ነገርኳቸው፤ ሁሉ ነገር እንዲከናወንላቸው ከፈለጉም እኔ በሰጠኋቸው ሥርዓት እንዲኖሩ አዘዝኳቸው። 24እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም፤ ትኲረትም አልሰጡትም፤ በዚህ ፈንታ በእልኽና በክፋት የተሞላው ልባቸው የመራቸውን አደረጉ፤ ወደ ፊት ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ። 25የቀድሞ አባቶቻችሁ ከግብጽ ከወጡበት ቀን አንሥቶ እስከዚህች ቀን ድረስ አገልጋዮቼን ነቢያትን እያከታተልኩ ከመላክ የተቈጠብኩበት ጊዜ የለም። 26ነገር ግን ያዳመጠኝም ሆነ ለትእዛዜ ትኲረት የሰጠ ሰው አልነበረም፤ ይልቁንም ከቀድሞ አባቶቻችሁ ብሳችሁ እልኸኞችና ዐመፀኞች ሆናችሁ።”
27“እንዲሁም አንተ ኤርምያስ ሆይ! ይህን ሁሉ ቃል ለሕዝቤ ትነግራቸዋለህ፤ ነገር ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸዋለህ፤ አይመልሱልህም። 28ይህ ሕዝብ ለእኔ ለአምላኩ የማይታዘዝና ከቅጣቱም ሥነ ሥርዓትን መማር የማይፈልግ ሆኖአል፤ በዚህ ምክንያት እውነት ጨርሳ ጠፍታለች፤ ስለ እርስዋ በአንደበቱ የሚያነሣ እንኳ የለም።”
በሂኖም ሸለቆ የተፈጸመ አሠቃቂ በደል
29“የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፥
ጠጒራችሁን ተላጭታችሁ በመጣል እዘኑ፤
ዛፎች በሌሉባቸው ኰረብቶች ራስ ላይ ሙሾ አውጡ፤
እኔ እግዚአብሔር ተቈጥቻለሁ፤
ሕዝቤንም ከፊቴ አሽቀንጥሬ ጥያለሁ።
30“የይሁዳ ሕዝብ ክፉ ነገር አድርገዋል፤ ይኸውም እኔ የምጠላቸውን ጣዖቶቻቸውን አስገብተው በውስጡ በማኖር ቤተ መቅደሴን አርክሰዋል። 31ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት እያቃጠሉ መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ በሂኖም ሸለቆ ውስጥ ‘ቶፌት’ ተብሎ የሚጠራ መሠዊያ ሠርተዋል፤ ይህም እኔ ያላዘዝኳቸውና በፍጹምም ያላሰብኩት ነገር ነው። #ዘሌ. 18፥21፤ 2ነገ. 23፥10፤ ኤር. 32፥35። 32ስለዚህ የዚያ ቦታ ስም የቤን ሂኖም ሸለቆ ወይም ቶፌት መባሉ ቀርቶ የዕርድ ሸለቆ ተብሎ የሚጠራበት ጊዜ ይመጣል፤ ሌላ የመቃብር ስፍራ ስለማይገኝ ያ ሸለቆ ራሱ የሕዝቡ መቃብር ይሆናል። 33ሬሳቸውም የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት ሲሳይ ይሆናል፤ አስፈራርቶ የሚያባርርላቸውም አይኖርም። 34ምድሪቱ ባድማ ትሆናለች፤ በኢየሩሳሌም መንገዶችና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ የሠርግ ዘፈን፥ የደስታና የሐሤት ድምፅ ከቶ እንዳይሰማ አደርጋለሁ። #ኤር. 16፥9፤ 25፥10፤ ራዕ. 18፥23።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 7: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997