ትንቢተ ኤርምያስ 26

26
የኤርምያስ ለፍርድ መቅረብ
1-2የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በይሁዳ እንደ ነገሠ ወዲያውኑ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቆመህ ከይሁዳ ከተሞች ሁሉ ለስግደት ወደዚያ ለሚመጡት ሕዝብ እኔ ያዘዝኩህን ሁሉ አንድ ነገር እንኳ ሳታስቀር ንገራቸው። #2ነገ. 23፥36—24፥6፤ 2ዜ.መ. 36፥5-7። 3ምናልባት ሕዝቡ አዳምጠው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ የሚመለሱም ከሆነ ከክፋታቸው ሁሉ የተነሣ በእነርሱ ላይ ላመጣ ያቀድኩትን ጥፋት እተዋለሁ።”
4እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ተናገር አለኝ፦ “እኔ እግዚአብሔር የሰጠኋችሁን ሕግ ባትከተሉና ባትታዘዙኝ፥ 5እናንተ ባታዳምጡአቸውም እንኳ አገልጋዮቼን ነቢያትን ደጋግሜ ወደ እናንተ ልኬአለሁ፤ 6ባለመታዘዛችሁ የምትቀጥሉበት ከሆነ በሴሎ ያደረግኹትን ሁሉ በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ ደግሜ አደርጋለሁ፤ የዓለም ሕዝብ ሁሉ የዚህችን የከተማ ስም እንደ መራገሚያ ይቈጥራል።” #ኢያሱ 18፥1፤ መዝ. 78፥60፤ ኤር. 7፥12-14።
7ካህናቱ፥ ነቢያቱና ሕዝቡም ሁሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ይህን ቃል ስናገር ሰምተውኛል፤ 8እግዚአብሔር እንድናገር ያዘዘኝን ሁሉ ተናግሬ እንደ ጨረስኩ በድንገት ያዙኝና “ሞት ይገባሃል!” ሲሉ ጮኹ፥ 9“ ‘ይህ ቤተ መቅደስ እንደ ሴሎ ይሆናል፥’ ብለህ በእግዚአብሔር ስም ትንቢት የተናገርከው ለምንድን ነው? ደግሞስ ‘ይህች ከተማ ትጠፋለች፥ በውስጥዋም ነዋሪ አይገኝባትም’ ያልከውስ ስለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁ። ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ በቤተ መቅደስ ተሰብስበው ዙሪያዬን ከበቡኝ።
10የይሁዳ መሪዎችም የሆነውን ነገር በሰሙ ጊዜ ከቤተ መንግሥት ወጥተው ወደ ቤተ መቅደስ መጡ፤ በቤተ መቅደሱም በአዲሱ የቅጽር በር ስፍራቸውን ያዙ። 11ካህናቱና ነቢያቱ ለመሪዎቹና ለሕዝቡ እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው የተናገረውን ሁሉ እናንተ ራሳችሁ ሰምታችሁታል፤ በከተማችን ላይ ክፉ የትንቢት ቃል በመናገሩ ሞት ይገባዋል።”
12እኔም ኤርምያስ ለመሪዎቹና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አልኩ፦ “በዚህች ከተማና በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ ይህን እናንተ የሰማችሁትን ቃል እንዳውጅ የላከኝ እግዚአብሔር ነው። 13አሁንም የአኗኗራችሁንና የሥራችሁን ሁኔታ ለውጣችሁ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይኖርባችኋል፤ ይህን ብታደርጉ በእናንተ ላይ ሊያመጣ ያቀደውን ጥፋት ይመልሰዋል። 14ስለ እኔ ጉዳይ እንደ ሆነ እነሆ በእናንተ እጅ ነኝ፤ ትክክልና ቀና መስሎ የታያችሁን ሁሉ አድርጉብኝ፤ 15ነገር ግን አንድ ነገር ብቻ በጥንቃቄ ልታረጋግጡ ይገባል፤ ይኸውም እኔን ብትገድሉኝ፥ እናንተና የዚህ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ ሁሉ ንጹሕ ሰው በመግደላችሁ በደለኞች ሆናችሁ ትገኛላችሁ፤ ይህን ማስጠንቀቂያ እንድሰጣችሁ ወደ እናንተ የላከኝ በእርግጥ ራሱ እግዚአብሔር ነው።”
16ከዚህ በኋላ መሪዎቹና ሕዝቡ፦ “ይህ ሰው የተናገረን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ስለ ሆነ ሞት አይገባውም” ሲሉ ለካህናቱና ለነቢያቱ ተናገሩ።
17ቀጥሎም ከሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ተነሥተው እዚያ ለተሰበሰበው ሕዝብ እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፦ 18“ሕዝቅያስ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን የሞሬሼቱ ነቢይ ሚክያስ የሠራዊት አምላክ የተናገረውን የትንቢት ቃል ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ዐውጆ ነበር፦
‘ጽዮን እንደ ማሳ ትታረሳለች፤
ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤
ቤተ መቅደሱም የተሠራበት ኰረብታ ዳዋ ይበቅልበታል።’ #ሚክ. 3፥12።
19ታዲያ ንጉሥ ሕዝቅያስና የይሁዳ ሕዝብ ሚክያስ እንዲገደል አደረጉን? አይደለም! ይልቁንም ሕዝቅያስ እግዚአብሔርን በመፍራት ምሕረት እንዲያደርግለት ተማጠነ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ሊያመጣ ዐቅዶት የነበረውን መቅሠፍት መለሰ፤ እኛ ግን አሁን አሠቃቂ የሆነ መቅሠፍት በራሳችን ላይ ለማምጣት ተዘጋጅተናል።”
20በቂርያትይዓሪም የሚኖር የሸማያ ልጅ ኡሪያ የተባለ ሌላም ሰው ነበር፤ ይህ ሰው ልክ እንደ ኤርምያስ በዚህች ከተማና በዚህች ምድር ላይ ጥፋት እንደሚመጣ በእግዚአብሔር ስም ትንቢት ተናግሮ ነበር፤ 21ንጉሥ ኢዮአቄምና መኳንንቱ፥ እንዲሁም የጦር አዛዦቹ ኡሪያ የተናገረውን በሰሙ ጊዜ፥ ኡሪያ እንዲገደል ንጉሡ ፈለገ፤ ኡሪያ ግን ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ፈራ፤ ወደ ግብጽም ሸሽቶ አመለጠ፤ 22ይሁን እንጂ ንጉሥ ኢዮአቄም የዓክቦር ልጅ ኤልናታንና ሌሎችም ሰዎች ወደ ግብጽ ወርደው ኡሪያን ይዘው እንዲመጡ አዘዘ፤ 23እነርሱም ወደ ንጉሥ ኢዮአቄም ይዘውት መጡ፤ ንጉሡም ኡሪያ እንዲገደልና በሕዝብ መቃብር ስፍራ እንዲጣል አዘዘ።
24እኔ ግን የሳፋን ልጅ አሒቃም ይከላከልልኝ ስለ ነበር ይገድሉኝ ዘንድ ለሕዝቡ ተላልፌ አልተሰጠሁም።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ