ትንቢተ ኤርምያስ 19
19
የተሰበረው ገንቦ ምሳሌ
1እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ሄደህ ከሸክላ ሠሪው ገንቦ ግዛ፤ ከሕዝቡና ከካህናቱ መካከል ታላላቆቹን መርጠህ ከአንተ ጋር አብረው እንዲሄዱ አድርግ። 2በሸክላ ስባሪ በር በኩል አድርገህ ወደ ሂኖም ሸለቆ ሂድ፤ በእዚያም እኔ የምነግርህን ቃል እንዲህ ብለህ ዐውጅ፦ #2ነገ. 23፥10፤ ኤር. 7፥30-32፤ 32፥34-35። 3‘የይሁዳ ነገሥታትና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የምነግራችሁን አድምጡ፤ እነሆ በጆሮው ለሚሰማው ሰው ሁሉ የሚዘገንን መቅሠፍት አመጣለሁ። 4ይህንንም የማደርገው ሕዝቡ እኔን ስለ ተዉና ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት በማቅረብ ይህን ስፍራ ስላረከሱ ነው፤ እነርሱም ሆኑ የቀድሞ አባቶቻቸው ከይሁዳ ነገሥታት ጭምር ስለ ነዚህ አማልክት የሚያውቁት ነገር የለም፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ንጹሖች ሰዎችን በመግደል ይህ ስፍራ በደም የተሞላ እንዲሆን አድርገውታል። 5ልጆቻቸውንም መሥዋዕት አድርገው በእሳት ለማቃጠል ለባዓል መሠዊያዎችን ሠርተዋል፤ ይህን እንዲያደርጉ አላዘዝኳቸውም፤ ከቶም ስለዚህ ነገር አላሰብኩም። #ዘሌ. 18፥21። 6ስለዚህ ይህ ስፍራ ቶፌት ወይም የሂኖም ሸለቆ መባሉ ቀርቶ የዕርድ ሸለቆ ተብሎ የሚጠራበት ጊዜ ይመጣል። 7የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ያቀዱት ነገር ሁሉ በዚህ ስፍራ እንዳይፈጸም አደርጋለሁ፤ ጠላቶቻቸው ድል እንዲነሡአቸውና በጦርነትም እንዲገድሉአቸው አደርጋለሁ፤ ሬሳቸውንም የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት እንዲበሉት አደርጋለሁ። 8ይህችን ከተማ የፍርስራሽ ክምር አደርጋታለሁ፤ በዚያ በኩል የሚያልፍ ሁሉ ይደነግጣል፤ በደረሰባት ችግርም ይገረማል። 9ጠላት ከተማይቱን ከቦ ሕዝቡን ለመጨረስ ያስጨንቋቸዋል፤ በዚህ ጊዜ ምግብ ሁሉ አልቆ ሕዝቡ ስለሚራብ እርስ በርሳቸው ይባላሉ፤ እንዲያውም ወላጆች የልጆቻቸውን ሥጋ ይበላሉ።’ ”
10ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አብረውኝ በሄዱት ሰዎች ፊት ያን ገንቦ እንድሰብረው አዘዘኝ፤ 11የሠራዊት አምላክ እንድነግራቸው ያዘዘኝም ቃል ይህ ነው፥ “ይህ የተሰበረ የሸክላ ገንቦ ተመልሶ ሊጠገን እንደማይችል፥ ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ በዚሁ ዐይነት እሰባብራለሁ፤ ሰዎች ሙታናቸውን የሚቀብሩበት ሌላ ስፍራ ስለማይገኝ በቶፌት ይቀብሩአቸዋል።” 12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በቶፌት ላይ እንዳደረግሁ በዚህ ከተማና በኗሪዎችዋ ላይ አደርጋለሁ፤ 13የኢየሩሳሌም ሕዝብና የይሁዳ ነገሥታት የሚኖሩባቸው ቤቶች፥ እንዲሁም በጣራዎቻቸው ላይ ለሰማይ ሠራዊት ዕጣን የሚታጠንባቸውና ለባዕዳን አማልክትም የወይን ጠጅ የሚፈስባቸው ቤቶች ሁሉ እንደ ቶፌት የረከሱ ይሆናሉ።”
14ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ቃሉን እንድናገርበት ካዘዘኝ ከቶፌት ተመልሼ መጣሁ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይም ቆሜ እንዲህ ብዬ ነገርኳቸው፤ 15“የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነርሱ እልኸኞች ሆነው ለቃሌ ስላልታዘዙ በዚህች ከተማና በዙሪያዋ በሚገኙ ስፍራዎች ሁሉ ይመጣል ብዬ ያስታወቅኹትን መቅሠፍት ሁሉ አመጣባቸዋለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 19: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997