የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 14

14
ስለ አሠቃቂው ድርቅ
1እግዚአብሔር ወደ ፊት ስለሚመጣው ድርቅ እንዲህ አለኝ፥
2“ይሁዳ በሐዘን ላይ ነች፤
ከተሞችዋም በሞት ጣዕር ላይ ናቸው፤
ሕዝብዋም በሐዘን ምክንያት በመሬት ላይ ተቀምጠው ያለቅሳሉ፤
ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔር ትጮኻለች።
3ሀብታሞች ውሃ ለማግኘት ሠራተኞቻቸውን ይልካሉ፤
እነርሱም ወደ ውሃ ጒድጓዶች ይሄዳሉ፤
ነገር ግን ምንም ውሃ ስለማያገኙ፥ ባዶ እንስራ ተሸክመው ይመለሳሉ፤
ተስፋ ቈርጠው ግራ ስለሚጋቡ፥
በሐዘን ራሳቸውን ይሸፍናሉ።
4ዝናብ ከመጥፋቱ የተነሣ፥ ምድር ትደርቃለች፤
ገበሬዎችም ተስፋ በመቊረጥ፥
በሐዘን ራሳቸውን ይሸፍናሉ።
5ሣር ካለመገኘቱ የተነሣ፥
አጋዘን እንደ ወለደች ግልገልዋን በሜዳ ላይ ጥላ ትሄዳለች።
6የሜዳ አህዮች ከውሃ ጥም የተነሣ፥
በየኰረብታው ጫፍ ላይ ቆመው እንደ ቀበሮ ያለከልካሉ፤
ምግብ ስለማያገኙም የማየት ኀይላቸው ይቀንሳል።
7ሕዝቤም ወደ እኔ እንዲህ በማለት ይጮኻሉ፤
‘ምንም እንኳ የበደላችን ብዛት በእኛ ላይ ቢመሰክርም፥
እግዚአብሔር ሆይ! በተስፋ ቃልህ መሠረት እርዳን፤
ከአንተ ርቀናል፤ አንተንም አሳዝነናል።
8የእስራኤል ተስፋ አንተ ብቻ ነህ፤
ከመቅሠፍት የምታድነንም አንተ ነህ፤
ታዲያ በምድራችን እንደ እንግዳ፥
ለአንድ ቀን እንደሚያድር መንገደኛስ የሆንከው ለምንድን ነው?
9ለምን ግራ እንደ ተጋባ ሰውና ሌላውን መርዳት እንደማይችል ኀይለኛ ወታደር ትሆናለህ?
እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን በመካከላችን ነህ፤
በስምህም እንጠራለን፤
እባክህ አትተወን።’ ”
10እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “ከእኔ ርቀው መሄድ ይወዳሉ፤ ራሳቸውንም አይቈጣጠሩም፤ ስለዚህ እኔ በእነርሱ ደስ አልሰኝም፤ የፈጸሙትን በደል ሁሉ በማስታወስ ስለ ኃጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ።”
11እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ “ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ 12እየጾሙ ቢጸልዩ እንኳ አላዳምጣቸውም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ሆነ የእህል ቊርባን ቢያቀርቡልኝ እንኳ በእነርሱ ደስ አልሰኝም፤ ይልቁንም በጦርነት፥ በራብና በወረርሽኝ እንዲያልቁ አደርጋለሁ።”
13እኔም እንዲህ አልኩ፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ነቢያቱ ‘ጦርነት ሆነ ራብ አይኖርም’ እያሉ ለሕዝቡ ይናገራሉ፤ ‘በምድራችን ዘላቂ ሰላም ብቻ እንደሚሰፍን እግዚአብሔር ተናግሮአል’ ይላሉ።”
14እግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ነቢያቱ በእኔ ስም ሐሰት ይናገራሉ፤ እኔ አላክኋቸውም፤ ትእዛዝም አልሰጠኋቸውም፤ አንድ ቃል እንኳ አልነገርኳቸውም፤ አየን የሚሉት ራእይ ሁሉ ከእኔ የተገኘ አይደለም፤ ትንቢታቸው ሁሉ የሐሰት ራእይ፥ መተት፥ ጣዖት አምልኮና ከሐሳባቸው ያፈለቁት ከንቱ ነገር ነው። 15እኔ ሳልካቸው ‘በምድራችን ላይ ራብም ሆነ ጦርነት አይመጣም’ እያሉ በስሜ ትንቢት የሚናገሩትን እነዚህን ነቢያት እኔ እግዚአብሔር በጦርነትና በረሀብ እንዲሞቱ አደርጋለሁ። 16ይህንንም የተነበዩላቸው ሕዝብ ሁሉ በራብና በጦርነት ይሞታሉ፤ ሬሳቸውም ሁሉ በኢየሩሳሌም ውስጥ በየመንገዱ ይወድቃል፤ የሚቀብራቸውም አይኖርም፤ ይህም በሚስቶቻቸው፥ በወንዶች ልጆቻቸውና በሴቶች ልጆቻቸው ሳይቀር በሁሉም ላይ ይፈጸማል፤ በበደላቸውም መጠን ተገቢ ቅጣታቸውን እሰጣቸዋለሁ።”
17ስለዚህ ጉዳይ እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ብዬ እንድናገር አዘዘኝ።
“ሕዝቤ እጅግ ቈስሎአል፤ በብርቱም ተጐድቶአል፤
ስለዚህ ዐይኖቼ ቀንና ሌሊት እንባ ያፈሳሉ፤
ባለማቋረጥም አለቅሳለሁ።
18ወደየመስኩ ብወጣ በጦርነት የተገደሉ ሰዎችን ሬሳ አያለሁ፤
ወደ ከተማም ብገባ በራብ ለመሞት የሚያጣጥሩ ሰዎችን አያለሁ፤
ነቢያትና ካህናት የራሳቸውን ጉዳይ ይከታተላሉ፤
ነገር ግን የሚያደርጉትን አያውቁም።”
ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ያቀረቡት ምልጃ
19እግዚአብሔር ሆይ! ይሁዳን ፈጽመህ ልትጥላት ነውን?
የጽዮንንስ ሕዝብ እንደ ጠላህ መቅረትህ ነውን?
ለመፈወስ እስከማንችል ድረስ፥
ይህን ያኽል እንድንጐዳ ማድረግህስ ስለምንድን ነው?
ሰላም እናገኛለን ብለን ተስፋ አደረግን፥
ነገር ግን ምንም መልካም ነገር አልገጠመንም፤
ፈውስ እናገኛለን ብለን ተስፋ አደረግን፤
ነገር ግን ሽብር እየበዛ ሄደ።
20እግዚአብሔር ሆይ! እኛ አንተን በድለናል፤
ስለዚህም የራሳችንንና የቀድሞ አባቶቻችንን ኃጢአት በፊትህ እንናዘዛለን።
21የተስፋ ቃልህን ሁሉ በማሰብ እኛን አትናቀን፤
ግርማህ የሚገለጥበት የክብር ዙፋንህ መኖሪያ የሆነችውን ኢየሩሳሌምን አታዋርዳት፤
ከእኛም ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን አስብ።
22ከአሕዛብ አማልክት መካከል
አንዱ እንኳ ዝናብ ማዝነብ አይችልም፤
ሰማይም በራሱ ፈቃድ ካፊያ አያወርድም፤
እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ!
ይህን ሁሉ የምታደርግ አንተ ስለ ሆንክ
እኛ ተስፋ የምናደርገው በአንተ ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ