ትንቢተ ኢሳይያስ 60
60
የወደፊቱ የኢየሩሳሌም ክብር
1ኢየሩሳሌም ሆይ!
ብርሃንሽ ስለ መጣ ተነሺና አብሪ፤
የእግዚአብሔርም ክብር በአንቺ ላይ ያበራል።
2እነሆ፥ ጨለማ ምድርን፥ ድቅድቅ ጨለማም ሕዝብን ይሸፍናል፤
ነገር ግን እግዚአብሔር በአንቺ ላይ ያበራል፤
ክብሩም በአንቺ ላይ ይገለጣል።
3ሕዝቦች ወደ ብርሃንሽ፥
ነገሥታትም ወደ ንጋትሽ ወገግታ ይመጣሉ።
4ቀና ብለሽ በዙሪያሽ ያለውን ሁኔታ ተመልከቺ!
ሁላቸውም ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤
ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤
ሴቶች ልጆችሽም በሞግዚቶቻቸው ክንድ ሆነው ወደ አንቺ ይመጣሉ።
5ይህንንም አይተሽ ፈገግታሽ በደስታ ይፈካል፤
ከባሕር የሚገኘው በረከትና፥ ከሕዝቦች የሚመጣው ሀብት የአንቺ ስለሚሆን፥
ከደስታሽ ብዛት የተነሣ ልብሽ ይፈነድቃል።
6ከምድያምና ከኤፋ የመጡት ግመሎች ምድራችሁን ሞሉት።
ወርቅና ዕጣን ይዘው ከሳባ የመጡት ሁሉ እግዚአብሔርን በከፍተኛ ድምፅ ያመሰግኑታል።
7የቄዳር የበግ መንጋዎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ፤
የነባዮት አውራ በጎችም ለመሥዋዕትነት ያገለግሉሻል፤
በመሠዊያም ላይ ለመሥዋዕትነት ለመቅረብ ተቀባይነት ይኖራቸዋል።
የተከበረውን ቤተ መቅደሴንም አስጌጣለሁ።
8እነዚህ እንደ ደመናና፥ ወይም ወደ ጎጆአቸው እንደሚመለሱ ርግቦች የሚያንዣብቡ እነማን ናቸው?
9የእስራኤል ቅዱስ፥ እግዚአብሔር አምላካችሁ
እናንተን ስላከበራችሁ ለእርሱ ክብር ሲሉ
በተርሴስ መርከቦች መሪነት ልጆቻችሁን ከብራቸውና ከወርቃቸው ጋር
ከሩቅ ቦታ ለማምጣት
ደሴቶቹ እኔን ይጠባበቃሉ።
10እኔ በቊጣዬ ቀጥቼሽ ነበር፤
አሁን ግን እራራልሻለሁ።
ባዕዳን ሕዝቦች ቅጽሮችሽን ይሠራሉ፤
ንጉሦቻቸውም ያገለግሉሻል።
11የሕዝቦችን፥ ሀብትና ንጉሦቻቸውን ያመጡ ዘንድ
በሮችሽ ሌሊትና ቀን ክፍት ይሆናሉ እንጂ አይዘጉም። #ራዕ. 21፥25-26።
12አንቺን የማያገለግሉ ሕዝቦችና መንግሥቶች ግን ፈጽመው ይጠፋሉ።
13ቤተ መቅደሴ ያረፈበትን ቦታ ለማስዋብ
የሊባኖስ ግርማ የሆኑት ዝግባ
አስታና ጥድ ወደ አንቺ እንዲመጡ ይደረጋሉ፤
እኔም የእግሬ ማረፊያ የሆነውን አከብረዋለሁ።
14የጨቋኞችሽ የልጅ ልጆች ወደ አንቺ ሲመጡ እጅ ይነሣሉ፤
የናቁሽም ሁሉ በእግርሽ ሥር ይንበረከካሉ፤
እነርሱም አንቺን “የእስራኤል ቅዱስ የእግዚአብሔር
ከተማ የሆነችው ጽዮን” ብለው ይጠሩሻል። #ራዕ. 3፥9።
15“ከዚህ በፊት የተተውሽና የተጠላሽ ሆነሽ
ማንም በአንቺ በኩል የማያልፍ የነበረ ቢሆንም እንኳ፥
የዘለዓለም መመኪያና በየትውልዱ ሁሉ መደሰቻ
እንድትሆኚ አደርግሻለሁ።
16ልጆች የእናታቸውን ጡት እንደሚጠቡ
የአንቺም ልጆች የሕዝቦችንና የነገሥታትን ሀብት በመውሰድ ይጠቀሙበታል፤
አንቺም እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽና ታዳጊሽ
ኀያሉ የያዕቆብ አምላክ መሆኔን ታውቂአለሽ።
17“እኔ በነሐስ ፈንታ ወርቅ፥
በብረት ፈንታ ብር፥
በእንጨት ፈንታ ነሐስ፥
በድንጋይም ፈንታ ብረት አመጣለሁ፤
ሰላምን እንደ አስተዳዳሪሽ
ጽድቅንም እንደ ገዢሽ አድርጌ እመድባለሁ።
18ከእንግዲህ ወዲህ በምድርሽ የዐመፅ ድምፅ
በድንበሮችሽም ጥፋት ወይም ውድመት አይሰማም፤
ነገር ግን ቅጥሮችሽን መዳን
የቅጥር በሮችሽን ምስጋና ብለሽ ትጠሪአቸዋለሽ።
19“ከእንግዲህ ወዲህ ፀሐይ በቀን፥ ጨረቃም በሌሊት አያበሩልሽም፤
ነገር ግን እግዚአብሔር ብርሃንሽ፥
አምላክሽም ክብርሽ ይሆናል። #ራዕ. 21፥23፤ 22፥5።
20እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ብርሃንሽ ስለሚሆን፥
ፀሐይሽ ከቶ አትጠልቅም፤ ጨረቃሽም ብርሃንዋን አትከለክልም፤
የመከራሽም ዘመን ያበቃል።
21ሕዝብሽ ጻድቃን ይሆናሉ፤
ምድሪቱን ለዘለዓለም ይወርሳሉ፤
እኔ እመሰገን ዘንድ እነርሱን የፈጠርኳቸውና
የተካኋቸው እኔ ነኝ።
22ከእነርሱ ጥቂቶቹ በሺህ የሚቈጠር ብዛት ይኖራቸዋል፤
ከእነርሱም ደካሞች የነበሩት ኀያል ሕዝብ ይሆናሉ፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ጉዳይ በጊዜው
ፈጥኖ እንዲፈጸም አደርጋለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 60: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997