የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 56

56
የሚታዘዙ ሁሉ ደኅንነትን እንደሚያገኙ
1እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ይላል፦ “የማድንበት ጊዜ ፈጥኖ ስለሚመጣና እኔ የምታደግበትም ጊዜ ስለ ቀረበ ፍትሕን ጠብቁ ትክክለኛውንም ነገር አድርጉ። 2ይህን የሚያደርግ፥ አጥብቆ የሚይዘው፥ ሰንበትን ሳይሽር የሚጠብቅ፥ እጁንም ክፉ ነገር ከማድረግ የሚገታ ሰው የተባረከ ነው።”
3ወደ እግዚአብሔር የተጠጋ ባዕድ ሰው “እግዚአብሔር ከራሱ ሕዝብ ይለየኛል” ብሎ አያስብ፤ ጃንደረባ የሆነ ሰው ልጅ ባለመውለዱ፦ “እንደ ደረቅ ዛፍ ነኝ” አይበል። 4እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰንበቴን ለሚያከብሩ፥ እኔ የምፈቅደውን ነገር ለሚመርጡና፥ በቃል ኪዳኔ ለሚጸኑ ጃንደረቦች 5ለእነርሱ በቤተ መቅደሴና በግቢዬ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የተሻለ መታሰቢያ እንዲኖራቸው አደርጋለሁ፤ የማይረሳ ዘላቂ መታወቂያም እሰጣቸዋለሁ።”
6ከባዕድ አገር መጥተው፥ ወደ እግዚአብሔር በመጠጋት እርሱን የሚወዱትንና የሚያገለግሉትን፥ የእርሱን ሰንበት ሳይሽሩ በማክበር ቃል ኪዳኑን የሚጠብቁትን ባዕዳንን እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፦ 7“እነርሱን ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አምጥቼ በጸሎት ቤቴም ደስ እንዲላቸው አደርጋለሁ፤ በመሠዊያዬም ላይ የሚያቀርቡትን የሚቃጠልና ሌሎችን መሥዋዕቶች ሁሉ እቀበላለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ቤቴ የሕዝቦች ሁሉ ጸሎት ቤት ተብሎ ስለሚጠራ ነው።” #ማቴ. 21፥13፤ ማር. 11፥17፤ ሉቃ. 19፥46።
8የተበተኑትን እስራኤላውያንን የሚሰበስበው ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከተሰበሰቡት ሌላ ሌሎችንም ወገኖች ወደ እነርሱ ሰብስቤ አመጣቸዋለሁ።”
የእስራኤል መሪዎች መወገዝ
9የባዕድ አገር ሕዝቦች እንደ አራዊት እየፈነጩ መጥተው ሕዝቡን ይውጡ ዘንድ እግዚአብሔር አዞአቸዋል፤ እርሱም እንዲህ ይላል፦ 10“የእስራኤል ጠባቂዎች ዕውሮች ናቸው፤ ሁሉም ዕውቀት የላቸውም፤ እነርሱም፥ እንደሚያንቀላፉ፥ እንደሚጋደሙ፥ እንደሚያልሙና መጮኽ እንደማይችሉ ውሾች ናቸው። 11እነርሱ በልተው እንደማይጠግቡ ውሾች ናቸው። የማያስተውሉም እረኞች ናቸው፤ ሁሉም በየራሳቸው መንገድ ይሄዳሉ፤ እያንዳንዱም የራሱን ጥቅም ያሳድዳል። 12እነርሱም፦ ‘ኑ ወይን ጠጅ እንፈልግ በጠንካራ መጠጥም እንርካ! ነገም እንደ ዛሬ ይሆናል፤ እንዲያውም በጣም የተሻለ ይሆናል!’ ይላሉ!”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ