ትንቢተ ኢሳይያስ 46
46
ስለ ባቢሎን ጣዖቶች
1“ቤልና ኔቦ የተባሉት የሐሰት አማልክት ያጐነብሳሉ፤
ጣዖቶቻቸው በጭነት እንስሶች ላይ ተጭነዋል፤
የተጫኑት ምስሎች ለደካማ እንስሳ ከባዶች ናቸው።
2የጭነት እንስሶቹ ከክብደቱ የተነሣ ከጭነቱ ጋር አብረው ወደቁ።
ጣዖቶቹም ራሳቸውን እንኳ ማዳን ስላልቻሉ ተማርከው ተወሰዱ።
3“ከማሕፀን ጀምሬ የጠበቅኋችሁና ከልደት ጀምሬ የረዳኋችሁ የያዕቆብ ልጆች የሆናችሁ፥ የእስራኤል ቅሪቶች! አድምጡኝ።
4አርጅታችሁ ጠጒራችሁ እስከሚሸብትበት ጊዜ ድረስ፥
የምጠብቃችሁ እኔ ነኝ፤
ፈጥሬአችኋለሁ፤ እንከባከባችኋለሁም፤ እረዳችኋለሁ፤
ከክፉ ነገርም እጠብቃችኋለሁ።
5“ከማን ጋር ታወዳድሩኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ?
ከማንስ ጋር አመሳስላችሁ ታወዳድሩኛላችሁ?
6አንዳንድ ሰዎች ኰረጆአቸውን ከፍተው ወርቅ እንደ ልባቸው ይመዛሉ፤
ብሩንም በሚዛን ይመዝናሉ፤
ጣዖት አድርጎ እንዲሠራላቸውም አንጥረኛ ይቀጥራሉ፤
ከተሠራም በኋላ እየሰገዱ ያመልኩታል።
7አንሥተውም በትከሻቸው ይሸከሙታል፤
በአንድ ቦታም ሲያኖሩት በዚያው ይቆማል፤
ካለበት ስፍራም መንቀሳቀስ አይችልም።
ማንም ሰው ወደ እርሱ ቢጸልይ መልስ አይሰጠውም፤
ወይም ማንንም ከጥፋት ሊያድን አይችልም።
8“እናንተ ዐመፀኞች! በአእምሮአችሁ ያዙት፤
በልባችሁም አኑሩት።
9እኔ ብቻ አምላክ መሆኔንና ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ዕወቁ፤
በቀድሞ ዘመን የተደረጉትን የጥንቱን ነገሮች አስታውሱ፤
እኔ አምላክ ነኝ፤ እኔንም የሚመስል ሌላ የለም።
10በመጨረሻ የሚሆነውን ነገር ከመጀመሪያው ጀምሬ ተናግሬአለሁ፤
ወደፊት ምን እንደሚሆን ከጥንት ጀምሬ ገልጬአለሁ፤
ዓላማዬ የጸና ይሆናል፤ የምፈቅደውንም አደርጋለሁ።
11ከወደ ምሥራቅ እንደ ነጣቂ ጭልፊት ያለውን እጠራለሁ፤
እርሱም ዓላማዬን የሚፈጽም፥ ከሩቅ አገር የሚመጣ ሰው ነው፤
የተናገርኩትን አደርጋለሁ፤
ያቀድኩትንም እፈጽማለሁ።
12“እናንተ ከእውነት የራቃችሁ
እልኸኞች አድምጡኝ።
13ጽድቄን አቀርባለሁ፤ ሩቅም አይደለም፤
ማዳኔ አይዘገይም፤
ኢየሩሳሌምን አድናለሁ፤
ለእስራኤልም ክብሬን አጐናጽፋለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 46: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997