የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 3

3
በኢየሩሳሌም ላይ የሚደርስ ሁከት
1እነሆ ጌታ የሠራዊት አምላክ፥ ሕዝቡ ኀይልና ብርታት አግኝተው የሚኖሩበትን ምግብና ውሃ፥ ሌላም ነገር ሁሉ ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ያስወግዳል። 2-3ጀግኖቻቸውን፥ ወታደሮቻቸውን፥ ዳኞቻቸውንና ነቢያታቸውን፥ ሟርተኞቻቸውንና ሽማግሌዎቻቸውን፥ የጦር መኰንኖቻቸውንና አማካሪዎቻቸውን፥ ጠንቋዮቻቸውንና የወደፊቱን እናውቃለን የሚሉትን ሁሉ ነቃቅሎ ያጠፋል። 4ገና ታዳጊ የሆኑና በዕድሜ ያልጠኑ ልጆችንም መሪዎች አድርጎ ይሾምባቸዋል። 5ሕዝቡም እርስ በርሱ አንዱ ሌላውን ለመጨቈን ባልንጀራ በባልንጀራው ላይ ይነሣሣል፤ ወጣቱ ሽማግሌውን አያከብርም፤ ተንቆ ይኖር የነበረውም ሰው ክብር ባለው ሰው ላይ ይታበያል።
6የቤተሰብ አባላት በአባታቸው ቤት አንዱን ወንድማቸውን መርጠው “አንተ ሌላው ቢቀር እንኳ የምትለብሰው ልብስ አለህ፤ ስለዚህ እባክህ አለቃችን ሁን፤ ፍርስራሽ ሁሉ በአንተ ሥልጣን ሥር ይሁን” ይሉታል።
7እርሱም በዚያን ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ “እኔም ብሆን በቤቴ ውስጥ የበቃ ምግብም ሆነ ልብስ ስለሌለኝ መፍትሔ ላስገኝላችሁ አልችልም! ስለዚህ መሪ አታድርጉኝ!” ሲል ይመልስላቸዋል።
8ኢየሩሳሌም ተሰናክላ በመንገዳገድ ላይ ናት፤ ይሁዳም ልትወድቅ ተቃርባለች፤ ምክንያቱም የሚናገሩትም ሆነ የሚሠሩት ሁሉ እግዚአብሔርን በመፈታተን ስለ ሆነ ክብሩን አቃለዋል። 9ለሚመለከታቸው ሰው ፊታቸው ይመሰክርባቸዋል፤ እንደ ሰዶም ሰዎች ሳይደብቁ ኃጢአታቸውን በግልጽ ይናገራሉ፤ በራሳቸው ላይ ጥፋትን ስላመጡ ወዮላቸው።
10ሁሉ ነገር ስለሚሳካላቸውና የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ስለሚያገኙ ጻድቃንን የተባረካችሁ ናችሁ በሉአቸው። 11ምንም ነገር ስለማይሳካላቸውና የክፉ ተግባራቸውን ዋጋ ስለሚያገኙ ለክፉዎች ወዮላቸው!
12ገንዘብ አበዳሪዎች ሕዝቤን ያራቊታሉ፤ አራጣ አበዳሪዎችም ይበዘብዙአቸዋል፤
ሕዝቤ ሆይ፥ መሪዎቻችሁ ያስቱአችኋል፤ የምትሄዱበትንም መንገድ ያጣምማሉ።
የእግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ መፍረድ
13እግዚአብሔር በፍርድ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦአል፤ በሕዝቡም ላይ ለመፍረድ ተዘጋጅቶአል። 14ስለዚህ የሕዝቡን መሪዎችና አማካሪዎች ወደ ፍርድ አቅርቦ እንዲህ ይላቸዋል፦ “የወይኑን አትክልት ቦታ ዘረፋችሁ፤ ከድኾች በተዘረፈው ሀብትም ቤታችሁን ሞላችሁ። 15የሕዝቤን ቅስም ልትሰብሩና ድኾችንም ልትበዘብዙ መብት የላችሁም፤ ይህን የተናገርኩ እኔ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነኝ።”
ለኢየሩሳሌም ሴቶች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
16እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የኢየሩሳሌም ሴቶች ኲራት አብዝተዋል፤ አንገታቸውን አስረዝመው በዐይናቸው ይጠቅሳሉ፤ አረማመዳቸውን ለውጠው የእግራቸውን አልቦ እያቃጨሉ በቀስታ ይራመዳሉ። 17እኔ በእነርሱ ራስ ላይ የቡሃና የቈረቈር በሽታ አመጣለሁ፤ የውስጥ ገላቸውም ይጋለጣል።”
18-23በዚያን ቀን ጌታ የኢየሩሳሌምን ሴቶች ጌጣጌጥ ማለት የእግራቸውን አልቦ፥ የጠጒራቸውን መሸፈኛ የአንገታቸውን ጌጣጌጥ፥ የጆሮአቸውን ጒትቻ፥ አምባራቸውን፥ የፊታቸውን መሸፈኛ፥ የጠጒራቸውን መሸፈኛ፥ በክንዳቸው ላይ የሚያደርጉትን ጌጥ፥ በወገባቸው ላይ የሚያስሩትን መቀነት፥ የሽቶ ጠርሙሳቸውን፥ ጥንቈላ የተጻፈበትን አሸንክታብ፥ የጣታቸውንና የአፍንጫቸውን ቀለበት፥ ለዓመት በዓል የሚሆነውን የክት ልብስ፥ መጐናጸፊያቸውንና ካባቸውን፥ የእጅ ቦርሳቸውን፥ መስታዋታቸውን፥ ከሐር የተሠራ የውስጥ ልብሳቸውን፥ ራስ ማሰሪያቸውንና ዐይነ ርግባቸውን ሁሉ ያስወግዳል።
24ስለዚህ በሽቶ ፈንታ ግማት፥ በጥሩ መታጠቂያ ፈንታ ገመድ፥ በጐፈሬ ፈንታ ቡሃነት፥ በመጐናጸፊያ ፈንታ ማቅ፥ በውበትም ፈንታ ጠባሳ መሆን ይመጣባቸዋል!
25ጐልማሶችሽ በሰይፍ፥ ኀያላንሽም በጦር ሜዳ ይወድቃሉ። 26የኢየሩሳሌም በሮች እርቃንዋን ሆና በልቅሶና በሐዘን እንደ ተቀመጠች ሴት ይሆናሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ